Tuesday, April 24, 2012

"ብቻዬን አይደለሁም"


የምን ያህሉሽ ሻይ ቤት
           ቀትር  ላይ  አባይ  ፏፏቴ  አካባቢ  ሙቀቱ  ልብ  ያቆማል !፡፡ ሙቀቱ  ግን  ያቃጥልም……. የሆነ ደስታ  የሚፈጥር  ስሜ ግን አለው ፡፡ ፏፏቴውን ለመጎብኘት አብረን ከተጓዝን ጓደኞቼ አንዱ በጣም ደክሞታል ፡፡  ጠምቶታልም፤ እናም በአካባቢው የሚኖሩ ትንንሽ  ልጆች  አስጎብኚዎቻችን  አረፍ  ልንል የምንችልበትና  ሻይ  ቡና ለማለት የምንችልበት ቦታ እንዳለ  በመጠቆም በነሱ መሪነት ሽቅብ ወደ ተራራው ወጣን፡፡
        አሁን  የአባይ  ፏፏቴ  አናት  ላይ  ጉብ  ብለናል ፡፡ ቁልቁል  የሚወረወረው  ጢስ  አባይ  ፏፏቴ  ልብ ይመስጣል ፡፡  ለእይታ  ምቹ  በሆነ  ቦታ ላይ አንድ  ግንድ ተደግፋ  በሳጠራ  የተከለለች  የወ/ ምን ያህሉሽ  ብቸኛ   ሻይ  ቤት  ትታያለች ፡፡   ማመን አቃተኝ…..የመግቢያ  በሯ  ጠባብ  ነው ፡፡    ተራ በተራ ወደ  ውስጥ  መዘለቅ  የግድ  ነው ፡፡ ሁለት  ጥንድ  ጓደኛሞች   የመስሉኝ   ተስተናጋጆች  ብቻ   ተቀምጠዋል ፡፡  እኛ  ስንጨመር  ቤቷ ሞላች ፡፡ / ምንትዋብ  እንግዶቿን  ለማስተናገድ  ተፍ ተፍ እያሉ ነው፡፡  ሞቅ ያለ ሀገራዊ  ሰላምታ  በመስጠት  ተቀበሉን …….ቤቷ ጠባብ ነች  በሁለት  ረድፍ መደዳውን ጨርቅ  የለበሱ  ድንጋይ  ተደርድረዋል ፡፡ ለመቀመጫነት ያገለግላሉ ግድግዳው  የሳጠራ ሆኖ  ውስጡን  ለማሳመር  በሀገሬ   ሸማኔዎች  የተጠበቡበት  የተለያየ  ባህልን  በሚያንፀባርቁ ጨርቆች  ተሸፍኗል ፡፡ እንዴት ያምራል መሰላችሁ…..! ፡፡ ፊት ለፊት  በሰፌድ  ላይ  የተቆራረጠ የአንባሻ  ዳቦ  በዳንቴል  ሹራብ  ተሸፍኖ  ተቀምጧል ፡፡ ሁለት ትልልቅ  ትኩስ  ሻይ  የተሞሉ ፔርሙዞች፣ አንድ  በለስላሳ  መጠጦች  የተሞላ   ሳጥን፣ እጅግ  በጣም  የሚያምር መልኩ  የተሰራ ረከቦት  በርካታ  የቡና  ሲኒዎችን  ደርድሮ  መሀል  ላይ  ጉብ  ብሏል !፡፡  የቡና  ጀበናው ትርክክ ብሎ  ከተቀጣጠለው  የከሰል  ምጣድ  ላይ  ተጥዶ  ሽቅብ  የሚተነፍሰው  እንፋሎት  የቡናውን  መድረስ እየጠቆመ ነው ፡፡  / ምን  ያህሉሽ  እድሜያቸው  ወደ  ሀምሳዎቹ  አጋማሽ  ላይ  የሚገመት አጠር ያሉ  ጠይም  መልከ  መልካም  የደስ  ደስ ላቸው  ናቸው ፡፡  እጣኑን ጨስ አድርገው  “እንኳን ደህና መጣችሁ ምን ልታዘዝ ..”  አሉን፡፡  ሁሉም  የፍላጎቱን  አዘዘ   የኔ  ምርጫ   ቡና  ነው፤ ምናልባት አላውቅም   በአባይ  ውሃ የተፈላ  ቡና ሊሆን ይችላል .! እየጣፈጠኝ  ጠጣሁ  ደገምኩ ቡናዬን ፉት እያልኩ ውስጤ አንድ ጥያቄ  አጫረ……፣  በዚህ  የሚያምር  ታሪካዊ  ቦታ  እንዴት  አንድ  ደረጃውን  የጠበቀ  ሆቴል  ወይም  ሎጅ  አይኖርም  ?  ፡፡ የክልሉ  መንግስት  አያውቀውም  ቦታውን ? እንዴትስ  የእኛ  ባለሀብት  ይሄን  ሃላፊነት  የሚወስድ  ጠፋ ?  ፡፡ አንድ ግን  ከሳጠራዋ  ሻይ ቤት በስተቀኝ  መሰረቱ  ተጀምሮ  የአረም  ዳዋ  ለብሶ  በጅምሩ  የቀረ  እንቅስቃሴ  አይቻለሁ ፡፡  በውስጤ ሲመላለስ  የነበረውን  ጥያቄ  ለወ/  ምን ያህሉሽ  አቀረብኩ
 “ይሄ እዚህ ጋር የሚታየው የህንፃ መሰረት ማነው የሰራው?” አልኳቸው
 “ ጊዜው  ቆይቷል አንድ ባለሀብት ነው መሰረቱን ጀምሮ በዛው ጠፋ ምክንያቱን ግን አላወኩም  ፡፡ታድያ  እንደው  የክልሉ  ባለስልጣናትስ  ወይም  ባለድርሻ  አካላት  ምንም  ሊያደርጉላችሁ  አልቻሉም ? "  ብዬ ሌላ ጥያቄ ጨመርኩ፡፡ /  ምን ያህሉሽ  በስራ  ተጠምደዋል  ብቻቸውን  ናቸው የሚያግዛቸው  የለም  ጥንካሬያውን  አደነኩኝ  ትንሽ  የእረፍት  ጊዜ  ሲያገኙ  ለጥያቄዬ  መልስ ለመስጠት ተዘጋጁ፡፡
"ምን ነበር ያልከኝ ? አዎ ምን ባክህ አንድ ጊዜ ስልጣናቸወን ባላውቅም ከመንግስት ተልከን ነው የመጣነውብለው  “ገበያው እንዴት ነው”  ምናምን  ብለው  ጠይቀውን  በቃ  በቅርቡ  እዚህ  ጋር  ትልቅ  መዝናኛ  ይከፈታል  አሉና  ሄዱ  ይኸው  እስከ  ዛሬ  የውሃ  ሽታ  ሆነው  እንደቀሩ ነው ፡፡ ምንም ያየነው ነገር የለም  “ እኛ  ግን  እንደ  አቅማችን  ጎብኚውን   እያገለገልን  ትንሽም  ቢሆንም  እየተጠቀምን  እንገኛለን፡፡ አሉና  አንገታቸውን  አቀረቀሩ…..፡፡ ትንሽ  ቆዩናም  እንዲህ  ሲሉ  ጠየቁኝ፡፡
         “ ልጄ ምናልባት ታገኛቸው እንደሁ ንገራቸው…….. ንገራቸው  ምነው ጠፋችሁ በልልኝ  ፡፡ አሉና  አደራም  ጭምር  አሳቀፉኝ  ፡፡ ጨዋታቸው  ይጣፍጣል  ብዙ  ልንጫወት  በወደድኩ  አዳዲስ እንግዶች  እየገቡ   ነው ፡፡  ወደ ዛው  መሄድ  አለባቸው  ከዚህ  በላይ  መቆየት አይችሉም፡፡  "ምነው ጠፋችሁ በልልኝ…..!”  አይደል  ያሉኝ  ጊዜው  እንዴት  ይሮጣል  …..ቀን ሳምንትን  ሳምንት  ወራትን ወራት  አመታትን   ሊደፍን  ጥቂት ቀረው ፡፡  ይኸው  የወ/ ምን ያህሉሽን  ቁጭት  ጥያቄና  አደራ በልቤ  መዝገብ   ተፅፎ   እንደተከደነ   አብሮኝ   እንደተቀመጠ   ነው   ምኞታቸው  ተሳክቶ  ይሆን ? ፡፡
*         *        *
               ሻይ ቤቷ ሞቅ ደመቅ  ብላለች ጓደኞቼ በግልና በጋራ ጉዳዮች ተጠምደው እየተጨዋወቱ  ነው፡፡ ድንገት ዞር ስል ከሳጠራ ሻይ ቤቷ ውጪ ከአባይ ፏፏቴው ፊት ለፊት በግማሽ ከመሬት የተቀበረ ድንጋይ ላይ  የተቀመጠች  ወጣት ልጅ ላይ አይኔ ተተክሎ ቀረ፡፡  ከላይ እስከ ታች ጥቁር  በጥቁር  የሆነ ቀሚስ ለብሳለች ፀጉሯም በጥቁር ሻሽ ተሸፍኗል፡፡ አዎ አልተሳሳትኩም ቅድም ከአራት ሴት ጓደኞቿ ጋር ከፏፏቴው ስር አይቻታለሁ፡፡ አሁን ግን ብቻዋን ነች፡፡ ጀርባዋና ለሻይ ቤቷ ሰጥታ አንገቷን ከጉልበቷ ቀብራ ተቀምጣለች፡፡ ምን ሆና ነው? ምን ይሆን የምታስበው? ለምንስ ከጓደኞቿ ጋር ተነጥላ መቀመጥ ፈለገች? ምክንያቷን ለመስማት ጓጓሁ እናም ፈራ ተባ እያልኩ አጠገቧ እንደደረስኩ እግሮቼ ላይ ቁጢጥ ብዬ ተቀመጥኩ እንዴት ብዬ ልጀምር…… ጨነቀኝ፤ እንደምንም ወኔዬን አሰባሰብኩና እንዲህ አልኳት፤
ጤና ይስጥልኝ የኔ እመቤት ምነው በሰላም ነው?አንገቷን ከጉልበቷ ላይ እንደደፋች ነው አልሰማችኝም አላየችኝም እጇን ነካ አድርጌ መልሼ ጠየኳት፡፡
እሙዬ ብቻሽን በሰላም ነው?”
አዎ በሰላም ነው ብቻዬን ግን አይደለሁም……..” ቀና ብላ አየቺኝ…….መልሳ አንገቷን አቀረቀረች…… የማለዳ  ፀሐይ የመሰለች ቀይ ቆንጆ ልጅ ነች፡፡ እድሜዋ ሀያዎቹ መጀመርያ ላይ እንደሚገኝ ገመትኩ፣ ቦግ ቦግ ብለው የሚያምሩት አይኖቿ ቀላ ብለዋል ትንንሽ የእንባ ዘለላዎችም እንደቋጠሩ እያየሁ ነው፡፡ አሁን የበለጠ ተረበሽኩ፡፡
"ታድያ ከማን ጋር ነሽ ?እእ ማለቴ……."
ጥያቄዩን አላስጨረሰቺኝም….
"ገብቶኛል ብቻዬን አይደለሁም አባይ እያጫወተኝ ነው፡፡ ፏፏቴው በዜማ እያዋዛ……ሽቅብ ወደላይ የሚተነው ጢስ ገላዬን እየዳበሰ…….ከማላውቀው ጥልቅ ስሜት ባህር ውስጥ ይከተኛል  እንዴት ብቻዬን እሆናለሁ?"፡፡
"ብቻዬን አይደለሁም"
ደገመቺልኝ……..  ቀና ብዩ ፏፏቴውን አየሁት ድምጹን ላጣጥመው ሞከርኩ እውነትም ዜማው ያምራል ቁልቁል እየተወረወረ  እንደ ሃረር የባቢሌ ድንዳዩች ተደራርበው  ከተቀመጡት  አለቶች ጋር ሲጋጭ ሆነ ደስ የሚል እንደ ትዝታ፤ወይም አንባሰል፤ወይም ደግሞ አንቺ ሆዩ፤ሲለው ደግሞ ዘለሰኛ፤ከፍ ሲል  የባቲን ቅኝት አይነት ድምጽ ያወጣል፡፡ሽቅብ  ወደላይ የሚተነው ጢስ በንፋስ እየታገዘ ሰውነቴን ዳሰሰው……..መላው አካሌን የሆነ ደስ የሚል ስሜት ወረረኝ፡፡ እውነት ብላለች "ብቻዋን አይደለቺም" ፡፡
ከዚህች ውብ ልጅ ጋር ጨዋታዩን መቀጠል ፈልጌያለሁ፡፡ እንዳርረብሻት ደግሞ ሰጋሁ፡፡ያልተመለሱ ጥያቄዋች ግን አሉ ደቂቃዎች በፍጥነት እየተጓዙ ነው……..፡፡ ድንገት ቀና ያለችበትን አጋጣሚ ጠብቄ እንዲህ አላኳት……
"ስምሽን ግን አልነገርሺኝም ማን ልበል?"
"ሰዓዳ እባላለሁ"
" ከየት ነው የመጣሺው ተማሪ ነሽ ሰራተኛ ?"
"ተማሪ ነኝ ተወልጄ ያደኩት ወሎ ደሴ ከተማ ነው፡፡ አሁን እዛው ደሴ የሁለተኛ ዓመት ተማሪ ነኝ "፡፡
" ገባኝ ተማሪ ነሻ……አሁን ትምህርት ተዘግቶ ነው? ማለቴ እንዴት ይሄን ቦታ ለማየት መጣሽ?"፡፡ ጥያቄዬን አዥጎደጎድኩት፡፡ ሰዓዳ እንደሰጋሁት ሳይሆን ካቀረቀረችበት ቀና ብላ ሙሉ ለሙሉ ፊቷን ወደኔ አዙራ ትረካዋን ቀጠለች፡፡
"ይኅውልህ ቅድም ያየሀቸው አራቱም ጓደኞቼ አንድ ላይ ነው የምንማረው፡፡ አንደኛዋ የአዲስ አበባ ልጅ ናት አንደኛዋ የሀዋሳ፤ሁለቱ ደግሞ የሃገሬ ልጆች ናቸው፡፡ ትምህርት ቤት አንድ ላይ ነው የምንማረው የምናድረውም፡፡ የምንዋደድ ጓደኞች ነን በሀሳብ እንግባባለን ፍላጎታችን በአጋጣሚ ተመሳሳይ ነው፡፡ ለታሪካዊ ቦታዎች፤ለተፈጥሮ ለኪነ-ጥበብ ልዩ ቦታ እንሰጣለን፡፡ እናም ሁልጊዜ አቅሙ ቢኖረን የሃገራችንን ታሪካዊ ቦታዎች የመጎብኘት ህልም ነበረን….፡፡ ህልማችንን ለማሳካት ከቡተሰብ፤ከወዳጅ ዘመድ፤ከጓደኛ ምናገኛትን ሳንቲም ማጠራቀም ጀመርን ገንዘብ ያዥ ግምጃ ቤት ደግሞ እኔ ነኝ….." አለችና ፈገግ አለች፡፡ ጥርሷ የወተት አረፋ ይመስላልየአባይን ጢስ አይነት…..! እኩል መደዳውን ተደርድረው ሰው ልብ ያማልላሉ፡፡ እንደገና ብትስቅልኝ ፈለኩ ቢሆንም ጨዋታዋ በለጠብኝ፡፡
"በናትሽ ጨዋታውኝ ቀጠይልኝ….."
"የዘንድሮ  ሳንቲም ብንለው ብናጠራቅመው……ልባችንን ሊሞላ አልቻለም….አንድ ቀን ግን አንድ አጋጣሚ ተፈጠረ……፡፡ ምን መሰለህ ያቺ የአዲስ  አበባዋ ጓደኛችን አክስቷ አውጪ ትመጣና "ልደትሺን አክብሪ" ብላ ዳጎስ ያለ ብር ትልክላታለች፡፡ እናም እንዴት እናክብር……? በሚል የተለያየ ሀሳብ ይቀርብ ጀመርእኔ ደግሞ ከልጅነቴ ጀምሮ ከጢስ አባይ ጋር ቀጠሮ ነበረኝ ዝም ብሎ ፊቴ ይመጣል እናም ያለ  ወትሮዬ  ከቴሌቪዥን መስኮት ፊት ለፊት አፍጥጫለሁ……! ቤተሰቦቼም አብረው ናቸው፡፡ የሳሎን ቤቱ የገድግዳ ሰዓት ከምሽቱ ሁለት ሰዓት መሆኑን እየነገረኝ ነው……….የምሽቱ የዜና አቅራቢ ሰላምታውን በማስቀደም…………."  ፡፡ አለችና ወደ ፏፏቴው ፊቷን መልሳ በጸጥታ ረጅም ተጓዘች……..ፈገግታዋ እንደ ሃምሌ ጉም ድንገት ሰማይ ላይ ተበተነ……የሚያምሩት አይኖቿ ትንንሽ ድቡልቡል የዕንባ ኳሶችን እንዳንጠለጠለ ነው……፡፡ ትንሽ ጊዜ ሰጠኋት
"እና ምን ሰማሽ..?" አልኳት ድምጼን ከፍ አድርጌ……
"ዜና አንባቢው "ርዕሰ ዜና" ብሎ ያቀረበው የጠቅላይ ሚኒስቴራችን የአባይን ወንዝ ለመገደብ የተጀመረውን እንቅስቃሴ ብስራት ነበር፡፡ ታውቃለህ! ከተቀመጥኩበት በድንጋጤ ዘልዬ ጮኩ…….ጭንቅላቴን በሁለት እጄ እንደያዝኩ ደርቄ ቀርቻለሁ፡፡ቤተሰቦቼ በሁኔታው ገርሟቸዋል፤ደንግጠዋልም……."፡፡ አለችና ትረካዋን ልትቀጥል ስትል አቋረጥኳት፡፡
"ሰዓዳ እኔም እኮ ገርሞኛል የብዙ ጊዜ ህልም የነበረው አባይ ሲገደብ፤ኤሌትሪክ ሲመነጭ……….እምልሽ ሀገራችን ከድህነት ስትላቀ……! ያስደስታል እንጂ ያስደነግጣል እንዴ…?"
"ይገባኛል ! እንዴት ይሄ ይጠፋኛል ብለህ ነው……?ስሜታዊ ያደረገኝ ግን ቅድም እንደነገርኩህ ከፏፏቴው  ጋር ቀጠሮ  ነበረን ሁልጊዜ በህልሜ ይታየኛል፤ያጫውተኛል፤ደስ የሚል ዜማውን በጆሮዬ ያንቆረቆረዋል……..እናም የነጠቁኝ ያህል ተሰማኝ………እዚህ ጋር ለመምጣት የምችለውን ሁሉ ጥረት አድርጌያለሁ  ምስጋና  ይገባውና  የጓደኛዬ ልደት ዛሬ ጥቅምት 24/2004 ዓም የልቤ ሊሞላ ቻለ፡፡ ምናልባት እየቆጠብን የነበረው ሳንቲም እስኪጠራቀም እኮ ግድቡ ስራውን ይጀምር ነበር………ቅድም አስጎብኚዬ እንደነገረኝ ከሆነ ዛሬ እድለኛ ሆነን ነው እንጂ ፏፏቴው ቀንሷል ፡፡ መገደብም ሆነ መክፈት ተችሏል ፡፡ ይኽው እኔና  አንተ  ደረስንበት……. ሁሉም ሰው ቢያየው ደስ ይለኝ ነበር……" ፡፡ አለቺኝ……. ፡፡ ቅድም ተበትኖ የነበረው  ፈገግታዋ  ተመልሷል፡፡በጀግንነት፤በድል አድራጊነት ስሜት ተሞልታለች….ከልብ ቀናሁባት
በርግጥ የሰዓዳን  ያህል  ባይሆንም እዚህ በመገኘቴ ደስተኛ ነኝ፡፡ ይሄን የመሰለ ታሪካዊ ቦታ፤የተፈጥሮን ጸጋ ከማየት የተሸለ ይኖር ይሆን…….?፡፡
               ከሰዓዳ ጋር  ዉለው  ቢያድሩ አይሰለችም ፡፡ አሁን ወደ  ቀድሞ  ጸጥታዋ ተመልሳለች ፡፡ አንድ የማላውቀው ስሜት ግን ውስጤ ቀርቷል፡፡ ባትለየኝ አብሬያት ብቆይ ተመኘሁ…….የሚሆን ግን አይመስለኝም፡፡ ጓደኞቿ ይጠብቋታል….እንዴት ደስ  የሚል የልደት በዓል ነው!፡፡ ምናልባት ጢስ ዓባይ ስር የልደት በዓሏን ያከበረች `ገሬ ሰው የመጀመርያዋ የሰዓዳ ጓደኛ ልትሆን ትችላለች……..መንፈሳዊ ቅናት አደረብኝ ፡፡
     የምን ያህሉሽ  ሻይ ቤት  የባህር  እጣን  ጭስ  ጢስ አባይን ሰንጥቆ  መአዛው  አወደንኝጓደኞቼ እዛው  ናቸው  መመለስ  አለብኝ፡፡   ሰዓዳን  በሃሳብ ተሰናበትኳት…. ልረብሻት አልፈለኩም……. አንገቷን  ከጉልበቷ  እንደደፋች ነው በጆሮዬ ደጋግሞ አንድ ነገር አቃጨለ "ብቻዬን አይደለሁም……….!" እንዲህም ያለች መሰለኝ፡፡
"ብቻዬን አይደለሁም"

1 comment:

  1. Best Story !! Can you edit የወ/ሮ ምን ያህሉሽ or ወ/ሮ ምንትዋብ :: These two names represent one name either w/o mintiwab or w/o minyahilush

    ReplyDelete