Wednesday, January 16, 2013

ሀዋሳ ቤሌማ……!



ሀዋሳ ቤሌማ……!
1
              “መጓዝ ማወቅ ነው…..!” ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1995 ዓም (ከአስር ዓመት በፊት መሆኑ ነው) በወርሃ መስከረም ላይ በአሁን ሰዓት ላይ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በዋና ከተማነት የምታገለግለውን ሃዋሳ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ ለማየት በቃሁ…..፡፡ በሃይቁ ላይ በነጻነት የሚደንሱ የተለያዩ አሶች፤ደስ በሚለው የማያቃጥለው ሞቃት አየሯ እና ሰማይ ላይ በደስታ የሚንሳፈፉ የተለያዩ አእዋፋት……! ባላቸው አቅም ሁሉ በፍቅር አና በደስታ እንግዶቿን የሚያስተናግዱ ህዝቦቿ ልብ የሚመስጥ ነበር…..፡፡ በዚያን ጊዜ ከተማዋ አቅም እንደሌለው…. ወላጅ  እንደረሳው…. የህጻን ልጅ ቁምጣ እዚም እዛም የተቦጨቀ የአስፋልትና የጠጠር መንገዶች፤በአሁን ሰዓት መሃል ፒያሳ ጎዳናን በኩራት ተኮፍሶ የሚታየውን የገብርኤል ቤተክርስቲያን ጨምሮ በጅምር የቀሩ ጥቂት ህንጻዎች፤የሃዋሳ ሃይቀርን ተከትለው እንደሚታዩት ግዙፍ የሾላ ዋርካ ዛፎች….እድሜ የጠገቡ አብዛኛውን አሮጌ ቤቶችና የቆዩ ትንንሽ ሆቴሎች…..ወዘተ…. የነበራት ሃዋሳ…. ውበትዋ ማርኮኝ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እየተመላለስኩ ደስታዬን አጣጥሜያለሁ……!፡፡ እነሆ ዛሬ ከሁለት አመት ቆይ በኋላ ዳግም ተመልሼ እዛው እገኛለሁ ፡፡ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ከተማዋ ተለውጣለች… አምራለች…!፡፡ በየጊዜው ለውጥ አለ የተጀመሩ ህንጻዎች አልቀው ሌሎች ተጀምረዋል፡፡በ1960ዎቹ አካባቢ 6ኪሎ ሜትር ብቻ ይሸፍን የነበረው የአስፋከልት መንገድ ዛሬ 56.6 ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡ ትንሽ የነበረው ወስጥ ለውስጥ የተቦዳደሰ መንገዶችዋ ዛሬ በኮብል ድንጋይ 18 ኪሎሜትር ያህል ተነጥፏል፡፡ ከሌሎች መሰል የሃገራችን ከተሞች በአንጻራዊነት ሲታይ በእድሜ ትንሽ ብትሆንም ተፈጥሮም እያገዛት እጅግ በፍጥነት እያደገች….. የሃገር ውስጥ እና የውጪ ቱሪስቶች ፤ ኢንቨስተሮች ቀልብ እየሳበች የመጣች ከተማ ሆናለች ፡፡ ይሄንንም ተከትሎ በህዝቦችዋ እና አካባቢው ሊፈጠር የሚችለውን የተለያዩ አሉታዊ እና አዎንታዊ ገጽታዎች እንዳሉ ሆነው በዚህ አጋጣሚ በጣም የማደንቀው ደራሲ ጋዜጠኛ እና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ ሶስተኛ ጆሮውን እና ሰስተኛ ዐይኑን ከፍቶ የታዘበውን የአሉታዊ ጓዳዋን በተለያዩ ጋዜጣና መጽሄት ላይ እያስነበበን ይገኛል ፡፡ ይሄን ለሱ እንተወውና ከተማዋ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ተዘዋውሬ ካየሁት ከሰማሁት፤ካነበብኩት በምስል በፎቶ ካስቀረሁት አዎንታዊ ገጽታዋ ለማለት ልሞክር፡፡
•••
ዛሬ የምናወራላት ሀዋሳ የዛሬ መጠርያዋን ከማግኘቷ ሀምሳ ዓመት በፊት “አዳሬ” የሚባል ስፍራ ነበር ትርጓሜውም “የግጦሽ መሬት” ማለት ነው እናም ከተማዋ የከተማ ወግ ስታገኝ ሀዋሳ ተብላ መጠራት ጀመረች ፡፡ ስሙ የተገኘው ከሃይቁ በመኮረጅ ሲሆን ቃሉም ሲዳምኛ ሲሆን “ሰፊ” ወይም “የተንጣለለ” እንደማለት ይሆናል ፡፡ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ እና ከባቢያዊ ሁኔታውን ስንመለከት የዛሬው የሲዳማ ዞን  ወይም በቀድሞው የሲዳማ አውራጃ በስተሰሜን የሚገኝ ቦታ ሲሆን ከሻሸመኔ ከተማ አስተደቡብ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ፡፡ከሀዋሳ በስተምእራብ የሀዋሳ ሃይቅ ተንጣሎ ሲገኝ በስተምስራቅ ደግሞ የወንዶ ገነት ተራራ አዘቅዝቆ ይመለከታታል ፡፡ ቦታው የስምጥ ሸለቆ አካል ሲሆን ልዩ ከሚያደርጉት መገለጫዎች ዋነኛው በዓመት ሁለት ጊዜ የዝናብ ወቅቶች ያለውና ለም መሬት በደን የተሸፈነ አካባቢ መሆኑ ነው፡፡
ይህ የዛሬዋን ሀዋሳ ነባራዊ ሁኔታ የለወጠው ታሪካዊ ክስተት የተፈጠረው በ1949 ዓም ነው ፡፡ ጉዳዩም የተከሰተው አጼ ሃይለስላሴ በ1949 ዓም በያኔው አጠራር የሲዳሞን ጠቅላይ ግዛት ለመጎብኘት በሚጓዙበት ወቅት የሃዋሳን አካባቢ ሲያቋርጡ በተመለከቱት የቦታው አቀማመጥና ተፈጥሮአዊ ጸጋ ተማረኩ፡፡ በወቅቱም የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ  ለነበሩት ለደጃዝማጅ (በኋላ ራስ) መንገሻ ስዩም ትእዛዝ አስተላለፉ……“ በዚህ ቦታ ዘመናዊ እርሻ ልማት እንዲከናወን አዲስ ከተማም እንዲሰራ እንዲሁም በሃይቁ ዳር ቤተመንግስት እንዲሰራ…..” የሚል ትእዛዝ ነበር፡፡ በመሆኑም ራስ መንገሻ ስዩም ያስተዳድሩት ከነበረው የአርሲ ጠቅላይ ግዛት ተዛውረው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛትን እንዲያስተዳድሩ ህዝቡንም እንዲያገለግሉ ሹመት አገኙ፡፡ ያኔ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ ይርጋለም ነበር ፡፡ ( በዚህ አጋጣሚ ከሃዋሳ ከተማ 43 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ የሚገኘው ይርጋለም ከተማ ብዙ ያልተዘመረለት የገጣሚና የውስጥ ቀዶ ሃኪም አብረሃም ፈለቀ (ቢላዋና ብዕር) የምትል የግጥም መድብል አለው)፤የነ ገጣሚ ደራሲ አብረሃም ረታ ፤የነ ገጣሚና  ጸሃፊ ተውኔት ደበበ ሰይፉ የትውልድ ከተማ ነው፡፡ ሄጄ የማየት እድሉ አጋጥሞኛል….! በተለይ ኪነ ጥበብን በሚያደንቅና  በዙርያው ላይ ላለ ሰው በሚያደንቃቸው የደራሲዎች ሃገር ሲገኙ ምን ያህል ደስታ እንደሚሰማው እኔ ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሁሉም በህይወት የሉም…… ምናልባት ወደፊት በተለይ ብዙ ስላልተዘመረለት ሁለገቡ ባለሙያ ስለ ዶክተር አብረሃም ፈለቀ ካየሁት ከሰማሁት ካነበብኩት ለማካፈል ለመጨዋወት እንሞክራለን) ፡፡
ራስ መንገሻ ይርጋለምን በሚያስተዳድሩበት ወቅት ከተማዋ ወደፊት ህዝቡ ሲጨምርና የማህበራዊ እኮኖሚያዊ ተቋማት ሲስፋፉ  አብሮ መስፋፋት ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ካጠኑ እና ካስጠኑ በኋላ ለውሳኔ በማቅረብ በ1960 ዓም የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማነት ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ መዛወሩ እውን ሆነ…..፡፡ ይህ አጋጣሚ ለሀዋሳ እድገት ትልቅ እድል የፈጠረ ሲሆን ለይርጋለም ከተማ እድገት መጎተት መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ምክንያቶች እንደዋንኛው የሚቆጠር ይመስላል፡፡ በዚህም የተነሳ የሀዋሳ ከተማ ታሪክ ወደሌላ ምእራፍ ተሸጋገረ ፡፡
                                      2
         መጓዝ ማወቅ ነው…..! ነበር አይደል ያልነው….!? በስሚ ስሚ በወሬ ከመስማትና አንብቦ ከመረዳት የመለጠ ካሉበት ቄዬ ርቀው በመጓዝ ተፈጥሮን በማድነቅ ፤ የህብረተሰቡን ማህበራዊ አኗኗር ፤ባህል አስተሳሰብ ፤የአበላል ፤የአለባበስ፤ሃይማኖታዊ ስርዓት መረዳት ወዘተ….እቦታው ድረስ በመሆን አምስቱንም የስሜት ህዋሳት ከማሰራት ባሻገር ሀገሬ ብለህ የምትጠራት ሃገርህ ከመውደድ በዘለለ በእውቀት የተሞላ መረጃ እንዲኖርህ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ገጽታውን ለይተህና ቀምረህ ለውጪው አለም እና ሀገር ውስጥ መረጃ እና ምስክር የሚሆን ካንተ በላይ ማን ያለ ይመስልሃል ? ማንም….!፡፡ እርግጥ ነው ሃገርህ ላይ በሚኖር መልካም አስተዳደር እጦት እሱን ተከትሎ በሚከሰት ሰው ሰራሽ ድህነት እንኳንስ ከሃገር ሃገር….መጓዝ ቀርቶ እንጀራ ፍለጋ ከቤት ወደ ስራ ቦታ መንቀሳቀስ አዳጋች የሆነበት ጊዜ ደርሰናል ፡፡ በዚህ በኩል በአንጻራዊነት ሲታይ የደርግ ዘመነ መንግስት የተሻለ መሰለኝ ቢያንስ በግዳጅም ቢሆን (ሀገርህን እወቅ) በሚል በየመስርያ ቤቱ በየትምህርት ቤቱ የሚቋቋም ክበብ እንደነበር…… እጅግ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው……ከፍተኛ ድጋፍም እንዳለው የሃገር ፍቅር ስሜት እንዲያድርብህ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው……! ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች ይጎበኙ ነበር እኔም ባለቀ ሰአትም ቢሆን የዚህ ፕሮግራም ተቋዳሽ ነበርኩ በርካታ ፓርኮችን ተፈጥሮአዊ መዝናኛዎችን ያየሁት ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ነው…..፡፡ አሁንም የለም ለማለት ባልደፍርም… ብዙ አልተሰራም ኧረ እንደውም አልተነካም….እርግጠኛ ነኝ ከሃገርህን እወቅና ጉዞ የበለጠ ሃይማኖታዊ ጉዞ እንደሚበልጥ አልጠራጠርም…. ያውም እንደዚህ አለም አንድ በሆነችበት ወቅት መረጃ እንደፈለገ ባስፈላጊው ሰዓት እየተገኘ ለምን እንዳልተሰራ ሁሉም ሊያስብበት…….፤ የሚመለከተው ክፍል ሊመልስ ይገባል ፡፡ ይልቅ ከደርዛችን ሳንወጣ ወደ ወጋችን እንመለስ….፡፡ መጓዝ ከአንድ ቦታ መንቀሳቀስ ትልቅ የውቀት ባህር ውሰጥ እንደመግባት ነው፡፡ በተለይ ለኪነጥበብ ሰው ይሄ አይነገርም……አንድ አጋጣሚ ላጫውታችሁ የሙዚቃ ደራሲ ገጣሚና ድምጻዊ ንዋይ ደበበ በአንድ ወቅት ከምኖርናት ከተማ ተገናኝተን በኪነጥነብ ዙርያ ሰፊ ጊዜ አሳልፈን ነበር ፡፡ ሃገር ውስጥ መጓዝ ተፈጥሮን ማድነቅ ታሪካዊ ቦታዎችን ማየት ይወዳል መውደድ ብቻ አይደለም በአንድ ወቅት ያጋጠመውን እንዲህ ሲል አጫወጠኝ…….፡፡
ከግቤ ባሻገር አለች እረ አንዲት ሰው
በፍቅር በናፍቆት ልቤን የምትወዘውዘው
አቦል ጀባ ብላ ቡናዋን ብቀምሰው
ልቤ ወደ ጂማ ሱስ አመላለሰው
ቤትሽ ጅማ ነው ወይ…….
ጅማ እንውረድ……… እያለ የአባ ጅፋርን ሃገር እያወደሰ የሚያቀነቅነውን ዘመን ተሸጋሪ የማይሰለች ዜማና ግጥም የደረሰው ከሃያ አንድ ዓመት በፊት ለኪነጥበብ ሙዚቃ ስራ በሄደበት አጋጣሚ በጉዞ ወቀት የጊቤ በረሃን አቋርጦ ጅማ ደርሶ ባለው ባየው ነገር ተገርሞ ተደምሞ…! ከዛም አልፎ ጅማ ድረስ ትርኢቱን ሊያሳዩ የሄዱትን የስራ ባልደረቦች ጨምሮ አንድ ታዋቂ የጅማ ሰው ቤት የእንኳን በደህና መጣችሁ የቡና ስነስርዓት በሚደረግበት ወቅት ቡናውን የምታፈላው የጅማ ቆንጆ ልጅ ውቧቷ ትህትናዋ ፤መስተንግዶዋ ስቦት እሷን ዋና ገጸ ባህሪ አድርጎ ጅማና አካባቢዋን የገለጸበትን ድርሰት እዛው ጽፎ እንደመጣ አጫውቶኛል፡፡ለዚህም ይመስለኛል በተለይ ተፈጥሮ….! ሃገርን እያወደሰ በስሜት  እያነሳ የጻፋቸው የሙዚቃ ግጥም ድርሰቶቹ ቀላልና የማይሰለቹ የሆኑት ወይም እውነት እውነት የሚሸቱት  እቦታው ከስሜት ሆኖ ስለሚጽፋቸው ይመስለኛል፡፡ ነውም ደግሞ…….እስቲ ልብ ብላችሁ አድምጧቸው፡፡
የነገር ዳርረዳርታዬ ወዲህ ነው ሃዋሳ ለዚህም ትመቻለች እውነት ትመቻለች….የነገ ሰው ይበለንና አጋጣሚዎችን እናነሳለን……..

Monday, December 24, 2012

የዝምታ ጩኽት…..!



                              የዝምታ ጩኽት…..!

       ከቀኑ 6፤00አካባቢ ተንቀሳቃሽ ስልኬ አቃጨለች፡፡ ጥቅምት 1/2005ዓም እነሆ ዛሬ የምናወራላት የትዕግስት አለምነህ ድምጽ ነው፡፡ ብዙ አወራን የትውውቃችን ሰበብ ይሄው የእሌክትሮኒክስ መረጃ መረብ (ፌስ ቡክ) ነው ፡፡እንደዋዛ በዚሁ መረጃ መረብ ከረጅም ጊዜ ጀምሮ ስሜቴን ሲነካኝ የምጽፋቸውን የግጥም ሙከራዎቼን በማድነቅ በማበረታታት በወዳጅነት በመጣመር ከሰነበትን በርካታ ወዳጆቼ መሃል አንዷ ሆና ተገኝታለች፡፡

በስልክ ቆይታችን አንድ የሚያስደንቅ የብስራት ዜና ነገረቺኝ…….፡፡ የበኩር ልጇ የሆነውን የግጥም መድብሏን ለማስመረቅ ዋዜማ ላይ ነች…..!፡፡ ቀጠለች በደስታዋ ቀንም እንድገኝና ከውስን ገጣሚያን መሃል እኔም የግጥም ስራዎቼን እንዳቀርብ መጽሃፏን እንድመርቅላት ጋበዘቺኝ ፡፡ ሌላ ደስታ…….!!፡፡እንኳንስ ለትልቅ ደረጃ፤ለአቅመ ምርቃት ለበቃ የግጥም መድብል ቀርቶ ሁለት ስንኝ ጽፎ ለሚያስነብበኝ ትልቅ ቦታ ሰጣለሁና የገጣሚ ትግስት አለምነህን ግበዣ በደስታ ተቀበልኩት፡፡



      ከገጣሚዋ ጋር በስልክ ከተገናኘን ከአንድ ሳምንት በኋላ በናፍቆትና በጉጉት ሲጠበቅ የነበረው የዝምታ ጩኅት የግጥም መድብል በይፋ የሚመረቅበት ቀን ደረሰ፡፡ጥቅምት 8/2005ዓም ቦታው አዲስ አበባ የሚገኘው የኢትዮጲያ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሀፍት ኤጀንሲ የቀድሞ ስሙ ወመዘክር በአዲሱ ህንጻ ትንሿ አዳራሽ እንደሚሆን ቀደም ብሎ ተነግሮኛል፡፡እናም ለዝግጅቱ ከአዲስ አበባ በምስራቅ አቅጣጫ 100 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ ከምትገኘው ናዝሬት (አዳማ) ከተማ ቀጥር ላይ በመነሳት ጉዞዬን ጀመርኩ፡፡

    ከሁለት ሰዓት የጉዞ ቆይታ በኋላ አዱ ገነት ስደርስ ከሰዓት በኋላ 9ሰዓት አካባቢ ሆኗል፡፡ ጊዜ የለም በቀጥታ ወደ ድግሱ ስፍራ አቀናሁ 10 ሰዓት አካባቢ የምረቃት ስነ ስርዓቱ ይጀምራል ፡፡ ከዛ በፊት ግን በምርቃት ስነ ስርዓቱ ላይ ለሚቀርቡ ግጥሞች ለመነጋገር የተመረጡ ገጣሚያን ቀድመው እንዲገኙ በተነገረን መሰረት ቦታው ላይ ደርሻለሁ፡፡

ከዚህ በፊት የማውቀው የቀድሞው ወመዘክር ህንጻ ከበስተጀርባው ግዙፍ ዘመናዊ ህንጻ ተገንብቶ መጠርያውም ተቀይሮ ጠበቀኝ፡፡ ለደቂቃዎች በትዝታ ወደኋላ መጓዜን አልደብቅም…..! ከረጅም አመት በፊት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ቆይታዬ ወቅት አልፎ አልፎ እገለገልበት ነበር እነሆ ዛሬ በልዩ አጋጣሚ በድጋሚ ለማየት በቃሁ…እንዴት ደስ ይላል……..!!!፡፡ በተለመደው ሁኔታ ዋናው በር ላይ የፍተሻ ስነ ስርአቱን አጠናቅቄ በጥበቃ ሰራተኞቹ ጠቋሚነት ወደ ትንሿ አዳራሽ ለመሄድ የትልቁን ህንጻ ደረጃ ወጥቼ እንደጨረስኩ በስተግራ ካለው በረንዳ ላይ ደጋሽዋን ገጣሚ ትግስት አለምነህን ለዓይነ ስጋ ለመጀመርያ ጊዜ ለመተያየት በቃሁ፡፡ ክብ ፊቷ ላይ የደስታ ብርሃን ተረጭቷል…..! አጠር ያለች ድንቡሽቡሽ ገጣሚ…..፡፡ በዚህ መልኩ አልጠበኳትም ግምቴ መስመሩን ስቷል.. እሷ ግን ቀድማ አውቃኝ ኖሮ እንደ ጸሃይ በሚያበራ ፈገግታዋ ተቀበለችኝ “እንኳን ደስ አለሽ” አልኳት ለፈገግታዋ መልስ ፡፡ ከገጣሚዋ ጋር አንድ ሰው ቆሟል …በቁመት አጭር ቀጭን ጸጉሩ ትንሽ ገባ ያለ ፍጥጥ ያሉና ንቁ የንስር አይን ያሉት …….! አላውቀውም ትኩር ብሎ ይመለከተኝ ነበር፡፡ በዝግጅቱ ላይ ተጋባዥ ሆኖ አንድ ግጥሙን ካቀረበልን በኋላ ግን ሰውየውን የማወቅ ጉጉቴ ጨመረ ……እናም ተዋወቅን ፡፡ ጋዜጠኛ እና ደራሲ ወሰን ሰገድ ገብረኪዳን ይባላል ፓ ፓ ፓ “ህዝብ ማለት” የሚል ርዕስ ያላትን ግጥሙን አንብቦል ወድጃታለሁ እራሴንም ቆም ብዬ እንድመለከት፤እንዳስብ ረድቶኛል “የቃሊቲ ሚስጥሮች” የሚል በእውነተኛ ታሪክ ላይ የሚያጠነጥን መጽሀፍ እንዳለው ሲነግረኝ ማመን አቃተኝ ፡፡ መጽሃፉን ለማንበብ አንድ ቀንና አንድ ለሊት ብቻ ነው የፈጀብኝ…..! አንድ ጊዜ ማንበብ ከጀመሩ ለማቆም ይከብዳል ልብ አንጠልጣይ እና በአንድ ወቅት በህይወት አጋጣሚው በእስር ቤት ስለደረሰበት ስላየው ሁኔታ ይተርካል….፡፡

                                                                               ©   ©   ©

                                     ሰዓት እየሄደ ነው የተጠበቁ ገጣሚያን አልመጡም አዳራሹም ጭር ብሏል የመጽሃፍ ምርቃት መሆኑን የሚነግረኝ አንዳችም አሻራ አጣሁ……“እንዴት ነው ነገሩ” አልኩኝ በልቤ….. “መቼም ይሄ የሃበሻ ቀጠሮ የሚባለው መጥፎ አመል እንደተጣባን እስከመቼ ይቀጥላል……?”ብቻዬን አወራሁ ፡፡ ተመልሼ ወደ በረንዳው ወጣሁ ገጣሚዋ በተንቀሳቃሽ ስልኳ እዚም እዛም ትደውላልች ቅድም በፈገግታ የተሞላው ፊቷ ጉም የሸፈነው ሰማይ መስሏል……አሁንም ከስልኳ ጋር ጆሮዋን እንዳጣበቀች ነው፡፡  ልረብሻት አልፈለኩም “ተመልሼ እመጣለሁ” በሚል በእጅ ምልክት አሳይቻት ደረጃውን ወረድኩ…..፡፡የቀድሞውን ወመዘክር ዙርያ ገባውን በትዝታ መነጥር መቃኘት ጀመርኩ…….አዲሱ ህንጻ በጣም ያምራል ወደ ውስጥ ዘልቄ ለማየት ባልታደልም እጅግ በጣም ዘመናዊ የሆነ በርካታ አገልግሎትም እንዲሰጥ ተደርጎ የተሰራ መሆኑን ለመገመት አያዳግትም፡፡ በህንጻው መውጫ በረንዳ ላይም እንዲህ የሚል ጽሁፍ በእምነበረድ ላይ ተጽፎ አነበብኩ፡፡ “ የብሄራዊ ቤተ መዛግብትና ቤተ መጽሃፍት ኤጀንሲ ዘርፍን በዘመናዊ መልክ በማደራጀት ጥናትና ምርምር እንዲስፋፋእና የመረጃ ሃብቶች ተጠብቀው ለትውልድ እንዲተላለፉ ለማድረግ የኤፌድሪ መንግስት በሰጠው ልዩ ትኩረት መሰረት ይህ ህንጻ ተገንብቶ በክቡር አንባሳደር ተሾመ ቶጋ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አፈ ጉባኤ ሰኔ 28/2000 ዓም በክብር ተመረቀ ” ይላል፡፡ ከፍተኛ ትኩረት እንደተሰጠውና በኤጀንሲ ደረጃ መቋቋሙ ገዢውን መንግስት ሳላመሰግን አላልፍም፡፡በዚሁ መልኩም በርካታ መጽሃፍት ቤቶች በርካታ ሙዚየሞች ቢከፈቱ ፍላጎቴም ምኞቴም ነው እንዲህ የምንጮህለት “ የሚያነብ ትውልድ…. ! ” የምንፈጥረው የተመቻቸ የማንበቢያ ቦታና ምቹ ሁኔታ ስንፈጥርለት ነው ፡፡ በዚህ አጋጣሚ ለኛው ልማታዊ ባለሃብቶች ከሰማይ ጠቀስ ዘመናዊ ህንጻዎቻቸው ቢያንስ አንዱን ክፍል ለቤተ መጽሃፍት ቢያውሉት መጽሃፍትን በመግዛት እንዲሁም ከለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመተባበር፤በመሰብሰብ የንባብ ባህልን ለማሳደግ ሃላፊነታቸውን እንዲወጡ ለመጠቆም እና በመማጸንም ጭምር እጠይቃለሁ ፡፡

                                                                          ©     ©    ©

                አሁን ተንቀሳቃሽ ስልኬ አቃጨለች ከገጣሚዋ የመጣ መልእክት ነው፡፡ተመልሼ ወደ ትንሿ አዳራሽ ገባሁ…….፡፡ቅድም ባዶ የነበረው አዳራሽ የተወሰኑ ገጣሚያን ተሰባስበው ጠበቁኝ ፡፡ ሁሉንም ማለት ይቻላል ለዐይነ ስጋ ለመጀመርያ ጊዜ መተያየታችን ነው፡፡ በዚሁ በማህበራዊ መረጃ ድህረ ገጽ (ፌስ ቡክ) በሚለጥፉት ወይም በሚያስተላልፉት የግጥም ስራዎቻቸው እንተዋወቃለን፡፡ ወደፊት ተስፋ የሚጣልባቸው ገጣሚያን መሆናቸውን መመስከር እፈልጋለሁ፡፡ ወቅታዊ የሆኑ የተለያየ ማህበራዊ ህይወትን የሚዳስሱ በቀላል ቋንቋ እና በምስል በተደገፈ የግጥም መልእክቶቻቸው እያዝናኑ ቁም ነገር የሚያስጨብጡ ናቸው…..፡፡ከዛ ባሻገር በዚሁ የመረጃ መረብ ስለሚለቀቁ የስነ ግጥም ስራዎች ጠንካራና ደካማ ጎን የግጥም አንባቢያንን ከመሳብ አኳያ እያደረጉት ያለውን አስተዋጽኦ ጠለቅ ያለ ሙያዊ አስተያየት ለመስጠት ጊዜ ወስዶ በስነ ጽሁፍ እና ስነ ግጥም በሳል እውቀት ያላቸው ባለሙያዎች ሃላፊነት ወስደው የበኩላቸውን እንዲወጡ መልእክቴን አስተላልፋለሁ፡፡

           ጀንበት ማዘቅዘቅ ጀምራለች …..የቀን ውሎዋን አጠናቃ ጠልቃ ከመሰወሯ በፊት ግን አርፍደው የመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች የምስልና የመቅረዘ ድምጽ መሳሪያዎቻቸውን በማስተካከል ተጠምደዋል ቅድም ባዶ የነበረው የመድረኩ ቀኝ ግድግዳ ጥግ የምረቃ የግጥም መጽሃፏን የፊት ሽፋን ምስል እና የምርቃቱን ብስራት የሚያመላክት ሸራ ተወጠረ፡፡ እየተንጠባጠቡ በሚመጡ የበዓሉ እድምተኞች ትንሿ አዳራሽ እየሞላች ነው ……!፡፡ አሁን በግጥም ደራሲዋ አማካኝነት ለግጥም አቅራቢዎች “የዝምታ ጩኅት” ተከፋፈለች….፡፡ እጄ የገባችው የግጥም መድብል የፊት ሽፋን ስዕል እጅግ በጣም ማርኮኛል፡፡አንዲት ውብ ኮረዳ ሴት በርካታ የቢራቢሮ ነፍሳት ወደ እሷ ሲተሙ ያሳያል…..፡፡ እንደሚታወቀው ቢራቢሮዎች  ለዓይን ከሚማርኩ አበቦች ጋር ልዩ ቁርኝት አላቸው ምግባቸውንም የሚያገኙት የመኖር ሕልውናቸው የተመሰረተው በአበቦች ላይ ይመስለኛል እኛ በማይገባን ለነሱ በሚጣፍጥ የማር ወለላ ከአበቦች ላይ ይቀስማሉ፡፡ እግረ መንገዳቸውንም የአበቦችን ዘር የማብዛት ስራ ይሰራሉ….፡፡ በምስሉ ላይ የምንመለከታት ውብ ሴት እንደ ቆንጆ አበባ እንውሰድና ቢራቢሮዎቹ ወደ ተምሳሌቷ ቆንጆ ይተማሉ፡፡ እንድም እንደ ስዕሉ ገለጻ በልጅቷ ውበት ተስበው በርካታ ወንዶች እየተከተሏት ነው…፡፡እሷ ደግሞ ለከጀላት ወንድ ሁሉ መሆን አትችልም አንዱን መምረጥ ይኖርባታል፡፡ በመሆኑም በቀላሉ ለሷ የሚሆንን ወንድ ለመለየት ይቸግራት ይሆናል፡፡ስለዚህ ከራሷ ጋር የምታደርገውን ሙግት፤ግጭት፤ፍጭት የነገሩን ከባድነት በቀላሉ በዓይነ ህሊናችን እንዲመጣ ያደርገናል ፡፡እንግዲህ እንደኔ  መገለጥ ፤መረዳት ወይም የማወቅ አቅም በወፍ በረር የታዘብኩት ይሄንን ነው፡፡ለግጥም መድብሏ የተሰጣት ርዕስና የሽፋን ስዕሉ አልገጠመልኝም ፡፡እስቲ ለግጥም መድብሏ የተሰጣት የርዕስ ግጥም ጭብጥ አንብበን እንመለስ፡፡

የዝምታ ጩኅት

እንዲያ ስለፈልፍ ከቁብ ያልቆጠረኝ

ተው ስል ስማጸነው ዞሮ እንኳን ያላየኝ

ተስፋዬን ቆርጨ ብሄድ ሳላወራው

በዝምታዬ ውስጥ ጩኅቴ ተሰማው፡፡

ያንተኑ ጨለማ ብትሰጠኝ ወርሼ

ከዝምታህ ጠበል ጠዲቅ ተቋድሼ

ዝም አልኩ ለፋሁ

ተከትዬ ጠፋሁ

የግርግሜ ኩራዝ ጭላንጭሏ ደክሞ

ብቸኛው ብቻዬ ብቻ ሲሄድ ከርሞ

ሰላሜን ካከኘሁ ከብቻህ ጋር ቆሞ

የቀረው ዘመኔን ልኑር በአርምሞ፡፡

• • •

    

                                                                    ©        ©        ©

             የምርቃት ዝግጅቱ ሊጀመር የተወሰኑ ደቂቃዎች ቀርተውታል፡፡የእለቱ የክብር እንግዳ የሆነው ዶክተር በድሉ ዋቅጅራ ጥቁር ቦርሳውን በትከሻው እንዳንጠለጠለ በፈገግታ ጠሞልቶ ወደ አዳራሹ ገባ፡፡ ረጅም ነው…. ሙሉ ወንዳ ወንድ ሰውነት የታደለ……እራሱ ላይ አንድም ጸጉር የለውም ግን ያምራል ሁላችንም በክብር ተቀበልነው…፡፡በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የስነ ጽሁፍ መምህር የሆነው ዶ/ር በድሉ ከዚህ በፊት ቤይሩት ላይ አስሪዎቿ የሞት አደጋ የደረሰባት የአለም ደቻሳን ልጆች ለመርዳት ዋቢ ሸበሌ ሆቴል በደጉ ኢትዮጲያዊ አባላት በተዘጋጀ የስነ ጽሁፍ ምሽት ላይ ተጋባዥ ሆኜ አንድ መድረክ ላይ የግጥም ስራዎቻችንን ለማቅረብ እና ለመተያየት በቅተናል ፡፡ እነሆ ዛሬ በቅርብ እርቀት በወንበር ተለያይተን ጎን ለጎን ተቀምጠናል….፡፡ ዶ/ር በድሉ ገጣሚ ነው “ሃገር ማለት የኔ ልጅ” የሚል የግጥም መድብል አለው፡፡ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ መድረኮች በጋዜጣና መጽሄቶች በኪነ ጥበብ ዙርያ ላይ እየሰጠ ያለው ሙያዊ ማብራርያ እና ጥናታዊ ጽሁፎቹ ታዋቂ እየሆነና በተለይ በስነ ጽሁፍ ዙርያ ላይ ለተሰማሩ ጀማሪ እና  ነባር ልምድ ያላቸው ጸሃፍት በሞራል ፤በሚያቀርቡት ጽሁፎች፤ግጥሞች የአርትኦት ድጋፍ  እየሰጠ ያለው አገልግሎት እንደ ዜጋ፤እንደ ባለሙያ እየተወጣ ያለውን ሃላፊነት ማድነቅ፤ማበረታታት እንዲሁም ተገቢውን እውቅና መስጠት “እውቀትህ ይብዛ ለሁሉ ትረፍ ” ብሎ መመረቅ ተገቢ ነው ፡፡ ይሄ ነገር ወጪ የለውም……. ትርፉ ግን ለሙሁሩ የተስፋ ስንቅ አስቋጥሮ በሞራል በጀመረው ተግባር እንዲቀጥል ይረዳዋል ፡፡

እንደዚህ አይነት አጋጣሚ ሊያመልጠኝ እንደማይገባ ውስጤን አሳመንኩት…፡፡ እናም እጄን እየዘረጋሁ

“ጤና ይስጥልኝ ዶ/ር”  አልኩት

“አብሮ ይስጥንኝ ” አለኝ አጸፋውን እጁን እየዘረጋ፡፡ እጅግ እንደማከብረው እንደማደንቀው አንድ የግጥም ስራውን እንዳነበብኩለት ነገርኩት፡፡ ከአንገቱ ዝቅ በማለት ምስጋናውን ገለጸልኝ፡፡ቀጠለናም፤…“አንተ ግን ከየት ነው የመጣኅው? የዚህ ከተማ ልጅ አልመሰልከኝም ” አለኝ ፡፡ መልሴን እየጓጓ ሙሉ ጆሮውን እየሰጠኝ…… ለጥቂት ጊዜም ቢሆን ከኔ ጋር ለማውራት ፈላጎት ማሳየቱ በድፍረት ላወራው አነሳሳኝ፡፡እኔም ግምቱ ትክክል እንደሆነ ለግጥም ምርቃት ከአዳማ(ናዝሬት) እንደመጣሁ በዝግጅቱ ላይም የግጥም ስራዎቼን እንደማቀርብ አጫወትኩት ፡፡ አሁን ሙሉ ለሙሉ ፊቱን ወደኔ አዞረ……….

“ስነ ግጥም ትጽፋለህ?” አለኝ፡፡

“አዎ እሞክራለሁ ቆይ እንደውም….” አልኩትና ለታዳሚው ለማቀብ ከያዝኳቸው አምስት ያህል አጫጭር የግጥም ስራዎቼን አቀበልኩት ፡፡የልቤ ምት ፍጥነቱን ጨምሯል…..! የሆነ የማላውቀው ዝብቅርቅ ያለ ስሜት እየተሰማኝ ነው፡፡የውስጤ ፍርሃት ግን ድብልቅልቅ ካለው ስሜቴ ገዝፎ ፊቴ ላይ ያሳብቃል…..፡፡ ከረጅም ዓመት ጀምሮ በል  ሲለኝ ስሜቴን ሲነካኝ የምተነፍሰው ግጥም በመጻፍ ነው፡፡በተለያየ ጊዜ በተለያየ ማህበራዊ ጉዳዮች ላይ የጻፍኳቸውን ግጥሞቼን ከአስራ ሶስት ዓመት በፊት በአዲስ አበባ የትምህርትና የስራ ቆይታዬ ወቅት ፒያሳ በሚገኘው የሩሲያ ሳይንስና ባህል አዳራሽ(ፑሽኪን አዳራሽ) ወርሃዊ የኪነ ጥበብ ምሽት ይካሄድ ነበር፡፡ እኔም በዛ ዝግጅት ላይ ለሁለት ዓመት በላይ ተካፍያለሁ በዝግጅቱ ላይ ከሚቀርቡ የተለያዩ የኪነጥበብ ስራዎች አንዱ  በተለያዩ የእድሜ ደረጃ ከጀማሪ እስከ ነባር ገጣሚያን የሚቀርቡ ስራዎች ናቸው፡፡በመሆኑም ማንኛውም ገጣሚያን ይመጥናል ብሎ የጻፈውን ግጥሞች ለማእከሉ ያቀርባል ፡፡የቀረቡት ጽሁፎች በዘርፉ ሙያ ባላቸው ገምጋሚዎች ታይተው ቅድመ ግምገማውን ያለፉ ግጥሞች በማስታወቅያ ሰሌዳ ላይ ይለጠፋሉ በቀጣይም ምሽቱ ከመካሄዱ አንድ ሳምንት ወይም ከዛ በፊት ቀድመ ምርመራውን ያለፉ ግጥምና ገጣሚያን እርስ በእርስ የሚገማገሙበት በሙያው ላይ ሰፊ ልምድ ያላቸው ሂስ የሚሰጡበት ….አስተያየት የተሰጡባቸው ግጥሞች ገጣሚያን ያለምንም ማመንታት ለማስተካከልና ለመማማር ፈቃደኛ የሚሆኑበት መድረክ ይዘጋጃል፡፡ገጣሚያን ከምሽቱ ቀን የበለጠ በጉጉት የሚጠብቁት ልባቸው በተከፋፈለ ስሜት የሚሞላበት ……..ለቀጣይ የስነ ጽሁፍ ህይወታቸው አቅጣጫን የሚለዩበት ወሳኝ ቀን በመሆኑ ገጣሚያን እንዲሁም እኔ ምን ጊዜም ሳስታውሰው እኖራለሁ……፡፡ የእህል ውሃ ነገር ሆኖ አዱ ገነትን ብሎም እንዲህ አይነት የኪነ ጥበብ ምሽቶች ፤ የስነ ጽሁፍ ባለሙያዎችን ርቄ በመቆየቴ ባገኘሁት አጋጣሚዎች መጽሃፍ ከማንበብ ግጥሞችን ጽፎ በአቅራቢያዬ ለሚገኙ ወዳጆቼ ከማሳየት በዘለለ የግጥም ስራዎቼን በሳጥን ቆልፌ ለረጅም ዓመታት ከቆየሁ በኋላ ዛሬ በልዩ አጋጣሚ በዘርፉ ከፍተኛ ትምህርትና ልምድ ባካበተው ከዶ/ር በድሉ እጅ ያውም በጣት የሚቆጠሩ ስራዎቼ እና ባለሙያው ፊት ለፊት ተፋጠው ቆመዋል ……….!፡፡ ይሄ ነው የፍርሃቴ ምንጭ ይሄ ነው ያለፈ የፑሽኪን አዳራሽ ጣፋጭ ትዝታዎቼን ያስታወሰኝ……..፡፡ በዚህ አጋጣሚ በወቅቱ የቀንዲል ቤተ ተውኔት መስራች ፤የሩሲያ ሳይንስና ባህል ማዕከል ሃላፊ የነበሩትን ገጣሚና ጸሃፈ ተውኔት አያልነህ ሙላት እንዲሁም ዝግጅቱ እንዲቃና ያለምንም ክፍያ በፍላጎት ሲሰራ የነበረውን መምህር ጌታቸው (ጌቾ) ሳላመሰግን ማለፍ አልፈልግም ፡፡ ጀማሪ ገጣሚያንን ፤የፊልም ባለሙያዎች፤የመድረክ ሰዎች፤ደራሲዎች ለመደገፍ ለማበረታታት ያደርግ የነበረው ጥረት የሚደነቅ ነበር ብዙዎቹ በወቅወቱ የነበሩ ልጆች ለትልቅ  ቁም ነገር ደርሰዋል……! ( በዚህ አጋጣሚ በዚህ ዙርያ ጣፋጭ የፑሽኪን አዳራሽ ትዝታዎቼን ዛሬ ላይ ለስኬት ስለበቁ ወዳጆቼ አንስቼ ለመጻፍ  እሞክራለሁ) የዛ ሰው ይበለን ፡፡

                                                                            ©    ©    ©

        ዝግጅቱ አልተጀመረም ዶ/ር በድሉ ዋቅጅራ አምስቱንም የግጥም ስራዎቼን አንድ በአንድ ካነበበ በኋላ ቀና ብሎ አየኝ…….. ተመልሶ ግጥሞቹን በሁለት ቦታ ለይቶ ያዛቸው ፡፡ የሚሰጠኝን አስተያየት በጉጉትና በጸጋ ለመቀበል ተዘጋጅቻለሁ ፡፡ ሶስቱን ግጥሞቼን ወደኔ በማስጠጋት  “እነዚህን ግጥሞች ወድጃቸዋለሁ ደስ የሚል ጭብጥ የሃሳብ አወራረድ፤ አሰካካቸው ሁሉ ቆንጆ ነው ፡፡ በተለይ ይህችን ግጥም በጣም ነው የወደድኳት ” አለኝና ነጥሎ አንዷን የግጥም ጽሁፍ አሳየኝ ፡፡ይህች ለብቻ ነጥሎ ያሳየኝ የግጥም ርዕስ “ያኔ ነው ፋሲካ ” የምትል ነች ፡፡ይህችን ግጥም ማስታወሻነቷ ስለሃገራችን ማህበራዊ ህይወት ፤ኢኮኖሚያዊ ሁኔታ ወቅታዊዊን የፖለቲካ አካሄድ ወዘተ በደፋር ብዕሩ ጽፎ ለሚያስነብበን ጋዜጠኛና የአንድ ጋዜጣ ዋና አዘጋጅ ለነበረው ወዳጄ ነው ያደረኩት በጋዜጠኝነት ህይወቱ ብዙ መንገላታት ብዙ ዋጋ እየከፈለ ነው ……..!አሁንም ለመክፈል ወደኋላ አይልም፡፡ እንደ አጋጣሚ ሆኖ ታሪኩን ሳጫውተው ጋዜጠኛውን ያውቀዋል ማወቅ ብቻም ሳይሆን አሁን አንድ መጽሄት ላይ አብረው ይሰራሉ ፡፡እናም የግጥሟ መልዕክት በትክክል ግቡን እንደመታ መሰከረልኝ ፡፡ ደስታዬ ወደር አልነበረውም “ በቃ አንተም ለማሳታወሻ ውሰዳት ”አልኩት በደስታ ተቀብሎ እግሩ ስር ከወሸቃት ጥቁሩ ቦርሳ ውስጥ ከተታት፡፡ እስቲ ግጥሟን አንብበን እንመለስ፡፡

ያኔ ነው ፋሲካ

ከንፈር የመጠጡ ያዘኑልኝ ሰዎች፤

ጽናቴን ብጠለል ባለሁበት ስከች፤

እብድ ነው እያሉ የለጠፉት ታርጋ፤

እውነት ስትወለድ የኛ ቀን ሲነጋ፤

ያኔ ነው ትንሳኤ ያኔ ነው ፋሲካ፤

ለታመኑት ታምነው የተሰዉ ለታ፡፡

• • •

        በግራ እጁ ለይቶ የያዛቸውን ሁለቱ ግጥሞቼን ማሰተካከል እንዳለብኝ ለግጥሞቹ የሰጠሁት ርዕስና ከግጥሞቹ ሃሳብ ጋር ምንም እንደማይገናኙ በተለይ የቃላት ምጣኔ ፤ዘይቤ አጠቃቀም፤ዜማ የሚሰብሩ አላሰፈላጊ ቃላት እንደተጠቀምኩ ደግሜ ደጋግሜ እንዳየው …የተለያዩ ደራሲያን ገጣሚያንን መድብሎች እንዳነብ በዛች በተጣበበች ደቂቃ ውስጥ በሙሉ ፍላጎት ሲያርመኝ ያሳየው ቀናነት ይበልጥ እንድወደው አደረገኝ፡፡ ምስጋናዬን ቃላት ብቻ የሚገልጸው አይመስለኝም ፡፡በፈለኩት ሰዓት በኪነ ጥበብ ዙርያ መነጋገር እንደምንችል ሙሉ ፈቃደኛ መሆኑን ደውዬ ማግኘት እንድችል የተንቀሳቃሽ ስልክ ቁጥሩን አቀበለኝ፡፡

የባንክ ባለሙያና ገጣሚ ትግስት አለምነህ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር ከ1994 ዓም ጀምሮ በቁጥረ 67 የሆኑ የግጥም ስራዎቿን “በዝምታ ጩኅት” ቋጥራ ለህትመት ከማብቃቷ በፊት ለዶ/ር ብሉ ማስገምገሟ በግጥም መድብሉ ዙርያ እያንዳንዱን ሙያዊ አስተያየት መቀበሏ ትክክለኛ እርምጃ ወስዳለች እላለሁ፡፡ ስለዚህም  በዚህ መድብል ውስጥ ስለተካተቱት የግጥም ስራዎች ቴክኒካል ጉዳዮችን አንስቶ ለመተቸት የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ድፍረቱ የለውም ይልቅስ በግጥሞቹ ጭብጥ ዙርያ ሊያስተላልፉ ስለሚፈልጉት መልእክቶች ግጥሞቹን ሲያነብ ስለተመቸውና ስሜቱን ስለነካው ጉዳዮች በቁንጽል እውቀቱ በመዳሰስ ቀሪውን ለአንባቢያን ለመተው ይመርጣል ፡፡ ከዛ በፊት ግን ማምሻውን እጥር ምጥን ብሎ በስኬት ስለተጠናቀቀው የምረቃት ስነስርዓት ፤ በስነ ስርዓቱ ላይ ስላጋጠሙት አስደሳች ገጠመኞች መቋጫ አበጅተን በሙሉ ሃይል ስለ ግጥም መጽሃፏ እንጫወታለን፡፡