Monday, July 9, 2012

ቴዲ አፍሮ ሰውየውን ለምን ወደደው?


         ቴዲ አፍሮ ሰውየውን ለምን ወደደው?
       

      ድምጻዊ፤ገጣሚና የሙዚቃ ደራሲ የሆነው ቴዎድሮስ ካሳሁን ቴዲ አፍሮ ለረጅም ጊዜ በተለያየ ምክንያት ከሙዚቃ አልበምና ከመድረክ ስራው ተለይቶ ቆይቶ በቅርቡ #ጥቁር ሰው; በሚለው አዲሱ የሙዚቃ አልበሙ ብቅ በማለት መላውን የሙዚቃ አፍቃሪ በወቅታዊ ብቃቱ መነጋገርያ እስከመሆንና በሙዚቃ አልበሙ ዙርያ የተለያዩ ስሜትና አስተያየቶችን በተለያዩ ጸሃፍትና የተለያዩ የማህበረሰብ ክፍሎች መወያያ ርዕስ ሆኖ መሰንበቱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው፡፡
         የዚህ ሙዚቀኛ ጽንፈኛ ደጋፊዎችና በገለልተኛ ሚዛን ባስቀመጡ አድማጮች መካከል በጋዜጣ፤በመጽሄት፤እንዲሁም በኤሌክትሮኒክስ የመረጃ መረብ በነበረ ፍጭት ግጭትና ሚዛናዊና ሚዛን አልባ አስተያየቶችን መቋጫ ለመስጠት የጉዳዩን ባለቤት የሆነውን ቴዲ አፍሮ በወረሃ ግንቦት 28/2004ዓም አዲስ አበባ በሚገኘው ሂልተን ሆቴል # የጥቁር ሰው ; አዲሱ አልበም ምርቃ በዓልን ምክንያት በማድረግ የተለያዩ ጥያቄዎችን ይዞ ብቅ ያለው የመንግስት የቴሌቪዥን ጣቢያ እንደሆነ የሚነገርለት ebs የካሳ ሾው ፕሮግራም ጋዜጠኛ ጋር እንግዳ በመሆን የነበረውን ቆይታ በተደጋጋሚ መመልከታችን፤ማድመጣችን ይታወቃል፡፡ እዚህ ላይ በተለያየ ምክንያት ከቀን ወደቀን በቁጥር እያነሱ የመጡት የግል የህትመት ሚድያዎች ምስጋና ይድረሳቸውና በቴሌቪዥን መስኮት ቃለ ምልልሱን ለማድመጥ እድሉ ላልገጠማቸው የጥበብ አፍቃሪያን የነበረውን ቆይታ እንደወረደ ለህትመት ማቅረባቸውን ከአንድም ሁለት መጽሄትና ጋዜጦች ላይ ለመመልከት ችያለሁ፡፡ ነገም ሌሎች በተለያየ መልክ ሀሳብና ትንታኔ በመስጠት ፤በመተቸት ቢያቀርቡ ተገቢ ነው ብሎ የዚህ ጽሁፍ አቅራቢ ያምናል፡፡
         የካሳ ሾው አዘጋጅ ጋዜጠኛ ሳሙኤል ካሳ ዝግጅቱን በማስተዋወቅ የቃለ ምልልሱን የቆይታ መድረክ መጋረጃውን በመክፈት ለድምጻዊው ምስጋና በማቅረብ ቃለ ምልልሱ የሚካሄድበት ቦታ የቴዲ አፍሮ ቤት መሆኑን በመጠቆም ጀመረ፡፡ ይህ ድምጻዊ ከሌላ ቀን በተለየ ሁኔታ በጥቁር ሰው የምረቃ በዓል ላይ ለብሶት የነበረውን በልዩ ሁኔታ ተሰርቶ ያሸበረቀ በሀገር ጥበብ ልብስ ደምቆ የንጉሳዊያን የክብር ዙፋን በሚመስለው ወይም በማይተናነሰው የሶፋ ወንበር ላይ በኩራት፤እግሩን እንዳነባበረ ተቀምጧል:: ከበስተጀርባው በጥሩ የፎቶ ፍሬም የተጠረዘ የግርማዊ ቀዳማዊ ንጉስ ኃይለስላሴ ፎቶግራፍ ይታያል፡፡ በስተቀኝ ግድግዳውን ተደግፎ በልዩ ሁኔታ የተሰራ በመስታወት ያሸበረቀ የእቃ መደርደርያ ውስጡ በተለያየ ጊዜና ወቅት የነበሩ የንጉሳዊያን ዘውድና መጠቀሚያ የመሰሉኝ ጌጣጌጦች በአይነት ተደርድረዋል፡፡ ከዚህ መደርደርያ አለፍ ብሎ ለአዲሱ አልበም መጠርያ የሆኑት የአጼ ምኒሊክ (ጥቁር ሰው) ምስል በቆዳ ላይ ተወጥሮ በእጅ የተሳለ ፎቶግራፍ ከግድግዳው ተሰቅሏል…….! እንዴት ደስ ይላል…….!፡፡
         ቴዲ አፍሮ የጋዜጠኛውን ጥያቄዎች በሙሉ ልብ በተረጋጋና  በሚመስጥ ሁኔታ መመለስ ቀጥሏል…..! ፡፡ የካሳሁን ልጅ ቴዲ……! ከዚህ ቀደም በተለያየ አጋጣሚ በጋዜጣ በመጽሄትና በተለያዩ የመረጃ መረቦች በሙዚቃ ስራዎቹና ተያያዥነት ባላቸው ጉዳዮች ከተለያዩ ጋዜጠኞች ጋር በነበረው ቆይታ ድምጻዊው የሚሰጣቸው መልሶች ለመስማትና ለማንበብ የታደልን የልጁን ግላዊ ስብዕና ጥልቀትና ምጥቀት፤ውስጣዊ ማንነቱን የሙዚቃ ህይወትና ከማህበተሰቡ ጋር ያለውን ጥልቅ ግኑኝነት አውቀን ቆይተናል፡፡ ዛሬ ወቅትና ጊዜያቶች አልፈው አሁን ላይ የደረሰበትን ደረጃ፤አስተውሎት፤ለሚጠየቀው ጥያቄ 'ሚሰጠው መልስ ጥንካሬ…..! ፤ምጥቀትና ቁጥብነት…..! ፤የቃላት ምጣኔ……!፤የሃረጎቹ አሰካክ….!፤እንደው ስሜታዊ ሆንክ ባትሉኝ ነፍስና ስጋ የለበሰ ስልቱን ጠብቆ በዜማ የተቀመረ አንድ የምወደው ወይም የምትወዱት የሙዚቃ ስልት ቃናው እየጣፈጠ ወደማይታወቀው ጥልቅ ሰማየ ሰማያት በመንፈስ የሚያስገባ፤የሚያደርስ ያህል አይነት እየተሰማኝ አደመጥኩት ደጋግሜ ሰማሁት………! ቴዲ ተለውጧል ፡፡ ሚስጥሩ ምን ይሆን……? ፡፡ ወደሌላ የግል አስተያየት ከመግባቴ በፊት ከጋዜጠኛው ጋር በነበረው ቆይታ ከበርካታ አስደናቂ ጥያቄና መልሶቹ መሃል ለዚህ ጽሁፍ መነሻ የሆነኝን ክፍል አንብበን እንመለስ፡፡