Thursday, May 10, 2012

የአለማየሁ እህት


ሳሊምቢኒ ጥቅምት 1 ቀን፣ 1890 በያዘው ማስታወሻ፣ አጤ ምኒልክ ትግራይ በነበሩ ጊዜ የተፈፀመ አንድ ታሪክ አንስቶአል።
በዚያን እለት ምሽት አጤ ምኒልክ ትግራይ ላይ ከተከሉት ንጉሳዊ ድንኳናቸው ተቀምጠው የቀጠሯትን አንዲት ሴት እየጠበቁ ነበር። እንደተጠበቀውም ማምሻው ላይ ወይዘሪቷ በሁለት አሽከሮች አጀብ በበቅሎ እየሰገረች ከአጤ ምኒልክ ድንኳን ደረሰች። በአካባቢው ብዙ ግርግር አልነበረም። ጥቁር ካባ የደረበች፣ በአበሻ ቀሚስ የደመቀች፣ ጠይም ረዘም ያለች ወይዘሪት ከበቅሎ እንደወረደች በጥድፊያ ወደ ንጉሱ ድንኳን እንድትዘልቅ ተደረገ። ይህች ሴት አልጣሽ ቴዎድሮስ ትባላለች። የአጤ ቴዎድሮስ ሴት ልጅ ስትሆን፣ የአጤ ምኒልክ ደግሞ የመጀመሪያ ሚስት ነበረች።
ንጉሱ ባዘዙት መሰረት ሁለቱ የቀድሞ ባልና ሚስት በአንድ ገበታ ላይ ለእራት ቀረቡ። የታሪክ መፃህፍት በደፈናው፣መሶብ ቀረበብቻ ብሎ ይገልፀዋል። ርግጥ ነው ይህ ቃል በቃል በበርካታ በመፃህፍት ተገልፆአል። ሁለቱ የቀድሞ ባልና ሚስት በዚያን ሌሊት አብረው ማደራቸውም ተፅፎአል። የራት ቆይታቸው ረጅም ነበር። ሆኖም ምኒልክና አልጣሽ ራት እየተመገቡ የተጨዋወቱት አልተመዘገበም። እንግዲህ ደራሲ እንደመሆኔ፣ በዚያን ምሽት የተነጋገሩትን የመስማት ችሎታና መብት አለኝ። ታሪክን በማጣቀስ በመሶቡ ዙሪያ በምናብ ላቆያችሁ፣

አጤ ምኒልክ እንዲህ ሲሉ ጠየቁ፣
ጤንነትሽ እንዴት ነው አልጣሽ?”
እኔማ ምን እሆናለሁ ብለሁ ነው? በእግዚአብሄር ፈቃድ አለሁ። የኛ ነገር እንዲህ መላ ማጣቱ ያንገበግበኛል እንጂ። በተለይ የአለማየሁ ነገር፣ ወንድም እንደሌለው፣ እህት እንደሌለው እንዲህ ሆኖ ሲቀር….”
ጥሩወርቅ ናት ያጠፋች። ይሂድ ብላ ፈቀደች።አባቱ እንዲማርለት ይፈልግ ነበርብላ ለእንግሊዞቹ ነገረቻቸው። ወላጆቹ ተፈቀዱ ምን ይደረጋል? ሁላችንስ በዚያን ግዜ ምን አቅም ነበረን? አምላክ የፈቀደው ሆኖአል…”
አልሆነላትም እንጂ ጥሩወርቅ  ልትለየው መች ፈለገች?”

አልጣሽ እንባዋን እያባባሰች ቀጠለች፣

“…የአለማየሁ ነገር ለመሸሻ የእግር እሳት እንደሆነበት አለ። ምንስ ቢሆን ለአንድ ወንድማችን መች እናንስ ነበር? ጊዜ ነው የጣለን። እርስዎስ ቢሆኑ ከኛ ጋር የወንድም ያህል አይደሉም እንዴ? የኔን ይተውት? ምን እንደበደልኩዎት ባለውእም ትተውኝ ሄደዋል። አባቴ ባባትዎ ላይ በፈፀመው ቂም ይዘው ይሆናል…”
ክፉ አትናገሪ አልጣሽ? የማይሆን ሆኖብኝ ትቼሽ መሄዴን አጥተሽው ነው? መቸ ጥሩ ሁኔታ ላይ ነበርኩ? ወርቂት አሳልፋ ለቴዎድሮስ ሰጥታ ልታስገድለኝ አልነበር? ምኑን ይዤ አንቺን ይዤ ልጓዝ? የችግር ሆኖ እንጂ ካንቺ የበለጠ ተገኝቶ መች ሆኖ?”
ቢፈልጉ እንኳ ከተረጋጉ በሁዋላአልጣሽ የት ደረሰች?’ ብለው በጠየቁ ነበር። እርስዎ ግን ሌላ አገቡ…”
ይኸው ፈልጌ አገኘሁሽ አይደለም እንዴ? ከልቤ ያልነበርሽ ቢሆን መች እጠራሽ ነበር? ደሞስ ብቻዬን የማደርገው መች ሆኖ? መኳንንቱ አሉ…”
እሱስ ልክ ብለዋል። ሆድ ቢብሰኝ ነው።ንጉሱ ጠርተውሻልብለው ሲሉኝ አልቅሻለሁ። የልጅነት ትዳራችን እንዳልታመመ አወቅሁ። እንዲያው ልጠይቆትና ከመረሃቤቴዋ ባላባት ልጅ ከባፈና ጋር እንዲህ መጣበቅዎ ለምን ይሆን? ምናምን አስነክታዎታለች ነው የሚባል…”

አጤ ምኒልክ ምላሽ ሳይሰጡ ዝም አሉ፣
እንዲህ ተጣብቀው ሲያበቁ ደግሞ ምነው ሳያነግሷት መቅረትዎ?”
ባፈና ስምንት ልጆች አሏት። ከሷ ጋር መንገስ የማይሆን ነበርሲሉ መለሱ።
ቢሆንም መቸም ይወዷት ነበር። መልኳ እንኳ ምንም የማይወጣላት ዘንፋላ ናት አሉ። በእድሜ ግን እናትዎ ትሆናለች ሰማን። ይህን ስሰማ አለቀስኩ። እኔ ምን ቢጎድለኝ ነው? ምን በድያቸው ነው? ብዬ ልቤ ተሰበረ።

አሁንም ምኒልክ ምንም ምላሽ አልሰጡም።

ባፈና ዙፋንዎን ለመጣል ተንኮል ሰርታ ነበር ሰማን…”
ሰዎች አሳስተዋት ነው
ስለሚወዷት ይሸፋፍኑላታል መቼም። አስነክታዎታለች እንጂ …”

እንደገና ምኒልክ ዝምታን መረጡ፣

ወልዳለዎት ነበር መባሉ እውነት ነው?”
ልጁ ባጭሩ ተቀጨ እንጂ ወልዳልኝ ነበር…”
ከጉራጌ ሴት የሚወለድ ኢትዮጵያን ለብዙ ዘመን ይገዛል የሚል ትንቢት ተነግሮ መኳንንቱ ሁሉ ከጉራጌ ሴት ተዋልዷል ይላሉ።አለች አልጣሽ በጎን አይኗ ንጉሱን እያየች፣

ምኒልክ ፈገግ አሉ። አልጣሽ ቀጠለች፣

እርሶም ይህን ትንቢት አምነው  ከቶሮ ልጅ ከወለተስላሴ ወልደዋል ሰማን።
ልክ ነው። የቶሮ ልጅ ሁለት ወልዳልኛለች…”

ከጥቂት ዝምታ በሁዋላ አልጣሽ ወሬ ቀየረች፣

ጣይቱስ እንዴት ናት?”
አጋዤ ናት…”
ልጅ ባለመውለዷ ይሰማት ይሆን?”
ጣይቱ ብርቱ ናት። ስለልጅ ሳነሳባት  14 ሚሊዮን የኢትዮጵያ ህዝብ ልጃችን ነው ትላለች። አምላክ ልጅ ከለከላት…”
እኔ እወልድሎት አልነበር? ችላ አሉኝ እንጂ
መች ችላ አልኩ? ይኸው መጣሽ አይደል? እግዚአብሄር ፈቃዱ ከሆነ አንቺ የምትወልጂው ልጅ ይነግስ ይሆናል…”

በዚያን ሌሊት አጤ ምኒልክና አልጣሽ አብረው ማደራቸውን ጳውሎስ ኞኞ መፅሃፉ ላይ ተርኮታል። እንደታለመውም ወይዘሪት አልጣሽ ከንጉሱ አረገዘች።ከሁለቱ የታላላቅ ነገስታት ዘር የሚወለደው ልጅ ኢትዮጵያን ለዘልአለሙ ይገዛልየሚል ትንቢት ከአዲስአበባ ጆሮ ደረሰ። አጤ ምኒልክም ይህን ተስፋ በማድረግ ከመጀመሪያ ሚስታቸው የሚወለደውን ህጻን በናፍቆት ይጠብቁ ጀመር። ህፃኑ ለመወለድ አንድ  ወር ያህል ሲቀረው ከአልጣሽ ወንድም ከመሸሻ የተላኩ ሁለት መልእክተኞች አዲስ አበባ በመምጣት አጤ ምኒልክን ለብቻ ለማነጋገር ጠየቁ። እንደተፈቀደላቸውም ገብተው አሳዛኝ መርዶ ለንጉሱ ነገሩ።

አልጣሽ አርፋለችየሚል ነበር።

አልጣሽ ከመውለዷ በፊት በእቴጌ ጣይቱ ትእዛዝ በመርዝ መገደሏን ሳሊምቢኒ ፅፎአል።

2 comments:

  1. አደም ጽሁፉ ጥሩ ነው ግን እቴጌ ጣይቱ ደግና ርህሩህ ሴት እንደነበሩ ይነገራል።ለውጭ ዜጎች ግን በተለይ ለጣሊያኖች መርዝ ነበሩ።ስማቸውን ለማጥፋት ብሎ የተጻፈ ይመስለኛል።

    ReplyDelete
  2. It is very interesting but un belivable!

    ReplyDelete