Thursday, May 10, 2012

እሳት ወይ አበባ


እሳት ወይ አበባ

 ሌት ከዋክብቱ  እንደ ፀደይ
አጥለቅልቆን  በቀይ አደይ
ሰማዩ  ሥጋጃ  አጥልቆ
ተሽለምልሞ  አንጸባርቆ
ፈክቶ አሸብርቆ  ደምቆ
በአዝመራ  በአጥቢያ  ዐፀድ  ሰፍኖ
የዓደይ  አዝርዕት  ተከሽኖ
በዕንቁጣጣሽ  ሰብል  ታጥኖ
ኢዮሃ  አበባዬ  ሆኖ፥
ጨረቃዋ  ከቆባዋ፥  ከሽልምልሚት  እምቡጧ
ብላ ከሰንኮፈንዋ፥ ተንዠርግጎ የእንኮይ ቡጧ፥
ድንግል  ጽጌ-ረዳ  ፈልቃ
ፍልቅልቂት  ድምቡል ቦቃ
ተንሠራፍታ  የአበባ  ጮርቃ፥
ታድያን  ብሌኑ  የጠጠረ
ባሕረ-ሃሳቡ የከረረ
የውበት ዓይኑ የታወረ
ልበ-ሕሊናው  የሰለለ
አይ፥ አበባ አይደለም አለ፤
አይ፥ እሳት አይደለም አለ፤
ያልታደለ።
ሰማይ  ጨለማ  ነው እንጂ፥  እሳት አደል ብሎ ካደ
እቶን  ባይኑ  እየነደደ።
ከዋክብቱ  እንደ  ችቦ
በነበልባል  ወርቀ  ዘቦ
ከፅንፍ  ፅንፍ  አውለብልቦ
ደመራው  እየተመመ
እየፋመ  እየጋመ
ደመና  እንደንዳድ  ሲነድ
መንጸባርቅ  ሰደድ  ሲወርድ፥
በራሪ  ኮከብ  ተኩሶ
በአድማሳት  እሳት  ለኩሶ
ይኸ እንደኔና  እንዳንቺው፥  የውበት ዓይኑ  የሰለለ
ሰማይ ጨለማ ነው እንጂ፥  እሳት እኮ አይደለም አለ፥
ያልታደለ።

ይቅር ብቻ  አንናገርም፥
እኔና  አንቺ  አንወያይም፤
ለውይይት  አልታደልንም
እንዲያው ዝም፥ እንዲያው ዝምዝም።
አበባ አንሆን ወይ እሳት
ተጠምደን  በምኞት  ቅጣት
ሰመመን  ባጫረው  መዓት
ዕድሜ አችንን እንዳማጥናት፤

እሳት አንሆን ወይ አበባ
በሕቅ  እንቅ  ስንባባ
ባከነች  ልጅነታችን፥ እየቃተትን ስናነባ
ሳንፈጠር  በሞትንባት
ሳናብብ  በረገፍንባት
ሳንጠና ባረጀንባት
አበባ ወይንም እሳት፥  መሆኑን ብቻ አጣንባት።
© © ©

ከጸጋዬ ገብረ መድኅን

2 comments:

  1. Thank you Adem. u are lucky coz ለነብስህ ጥሪ ምላሽ እየሰጠህ ነው:: ታነባለህ ትጽፋለህ! በርታ!!

    ReplyDelete
  2. እግዜር ይስጥልኝ ወዳጄ አደም! ይልመድብህ።

    ReplyDelete