,,,,እነሆ
በረከት ወ ስበሃት ,,,,,,,
አስራ አራት ዓመት ወደኋላ ልመልሳችሁ ነው…….
ጨርቆስ አካባቢ አንዲት ውብ ጓደኛችን ቤት ታድመናል ሁላችንም አንድ አይነት ፍላጎት ፤አንድ አይነት አስተሳሰብ እና ለኪነ-ጥነብ
ልዩ ፍቀር ያለን ጓደኞች፡፡ አንድ ትልቅ እንግዳ ልንቀበል ነው፡፡ ነገሩ ምን መቀበል ብቻ ምናልባት ስለሱ ተሰምቶ፤ተወርቶ የማያልቀውን
ዝናውን እውቀቱን ህይወቱን ብቻ ሁሉ ነገሩን ለመቋደስ፡፡ ቤቷ ጠባብ ነች ግን ትበቃናለች፡፡ ቆይ ስንት ነን ዳንኤል፤ ዳዊት፤አለም፤
እኔ…….. ማ ቀረ? እንግዳው ጋሽ ስብሃት እንግዳውን ይዞት የሚመጣው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ፡፡
አዎ በህይወቴ
እጅግ ደስ ያለኝ ቀን ቢኖር ስብሃትን የዛን ቀን በአካል ያገኘሁት እለት ነው፡፡ሁሉ ነገር ተዘጋጅቷል፡፡ ምሳ ፓስታ ነው የተጋበዘው
ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡
ምግብ ሰሪዋን ምን ብሎ እንዳመሰገናት ልንገራችሁ፡፡
"አለም" ጠራት ፡፡ "እኔና ቤቴ ግን አግዚያብሄርን እናመሰግናለን"፡፡
ሁላችንም
የቻልነውን፤ውስጣችን የሚመላለሰውን ነገሮች ሁሉ መጠየቅ ጀመርን ሰውየው ይመልሳል……….
"እስቲ ስለ ኤሚ ዞላ አጫውተን"
ዳዊት ነው ጠያቂው ስለፈረንሳዊው ታዋቂ ደራሲ በደስታ ይመልሳል የደራሲውን
ግልጽነት፤ደፋርነት አነጋጋሪነት የቃላት አመራረጥ ዘዴውን…….. እኔም ቀጠልኩ
"ጋሽ ስበሃት"
"ለበይክ" አለኝ
"ስለ ቼኮቬራ አውርተህ አትጨርስም ለኔም ብታካፍለኝ" ፡፡ ጠየኩት፡፡
ድንገት ከተቀመጠበት ፍራሽ ላይ ብድግ ብሎ ቆመ፡፡
" ጥሩ ጥያቄ ነው ቼኮቬራን ግን ቁጭ ብዬ አይደለም የማወራልህ
አጥንቱ ይወጋኛል"
አለና "ቼ..ለኔ ልዩ ሰው ነው መልዓክ አይነት…. ግን ቆይ
ሃኪም እንደነበር የሚያውቅ ሰው አለ ከመሃላችሁ?" ጠየቀን….. መልስ የለም፡፡ የሚመስጥ ታሪኩን አውርቶ ሲጨርስ እ….እፎይ
ብሎ ተቀመጠ፡፡ መልሶ እኔን ጠየቀኝ
"አንተ ግን ሙስሊም ነህ ?"
"አዎ ነኝ"
"ቁርአን አንብበሃል?"
"አላነበብኩም"
"ቀረብህ
ኢቅራ….." አለኝ፡፡
እሱ ኮ…ቁርአንን
ፉት አደርጎ አንብቦታል ማንበብ ብቻ ሳይሆን የእስልምናን አመጣጥ የነብዩ መሀመድን፤ገድል፤ስርአት፤አስተምሮት፤ጠንቅቆ እንደሚያውቅ፤
እንደሚወደው፤ ታሪኩ እንደሚመስጠው አጫወተኝ ተገረምኩ፡፡ ዳንኤል ሰለሰ………
"ጋሽ ስበሃት"
"አቤት ወዳጄ"
"ስለ ውበት ያለህን አመለካከት እባክህ
ጀባ በለኝ"
"መረሃባ ዳኒ ቆይ የሴት ጡት ጫፉን ትኩር ብለህ አይተህ
ታውቃለህ?"
"ኧ…..ረ አላውቅም"
ደነገጠ …. እኔም ደንግጫለሁ…. ሁላችንም ፊታችንን ወደ ቤቷ ባለቤት
ጓደኛችን አለም አዞርን ሴት እሷ ብቻ ነች……..ጋሽ ስብሃት ግን አልገረመውም ፤አልደነቀውም ፤ አልደነገጠም ፡፡ ቀጠለ…..
"በቃ ውበት ማለት በተወጠረ የሴት ጡት ጫፍ ላይ የምታየውን አይበገሬነት
ይመስላል "
ነጻነቱ ገረመኝ በወሬ የሰማሁትን በአይኔ አየሁት፡፡ አንድ ጥያቄ መጠየቅም
ፈለኩ
"ጋሽ ስበሃት"
"ለበይክ"
"ለበይክ" ማለት ( አቤት) እንደማለት ነው በአረብኛ፡፡
"አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ነው"
"ማለፊያ ጠይቃ"
"ብዙ ጊዜ ስለ ውቤ በረሃ አንስተህ አትጠግብም ደግሞ ወቤ
በረሃን እንደወረደ ማውራት፤ማንሳት ትወዳለህ ምንድነው ሚስጥሩ?"፡፡ አልኩት መልሱን እየጓጓሁ፡፡
"መርሃባ
ና እጅህን አምጣ"
አለኝና የመጨረሻ ጣቱን ቀስሮ ሌሎቹን አጥፎ ወደኔ ዘረጋቸው፡፡እኔም እሱ እንዳደረገው
ተከተልኩት፡፡ የመጨረሻ ጣቶቻችንን እንዳቆላለፍን ከሰኮንዶች ቆይታ በኋላ አላቀን ሳም አደረግናቸው እንደልጅነታችን……
"አሁን የምወደውን ጥያቄ ጠየክ ይኅውልህ ውቤ በረሃ
ለኔ ገነት እንደማለት ነው፡፡ የዋህነትን ፤ቀጥተኛነትን ፤የምታውቅበት የሚገባህ ዘመን ነው፡፡ ያኔ ደንሰህ፤ጨፍረህ፤ሀጢያትህን አስነጥሰህ
የምትመለስበት ቦታ ፡፡ ብር የለም ያኔ የፈለከውን ግን ታገኛለህ መደነስ ካማረህ ደንሰህ፤መጠጣት ካማረህ ጠጥተህ፤ሴት ማቀፍ ካማረ
አቅፈህ ትመለሳለህ በነጻ፡፡ እኔማ በዚህ እታወቃለሁ፡፡ መንግስት የሚከፍለኝ ብር አይበቃኝማ ታድያ እሞታለሁ ፡፡ አንድ ባለ ሱቅ
ነበር..ቆይ ስሙ ጠፋኝ እንዴ……? አዎ ፈድሉ ይባላል ባለ ሱቅ ነው ደንበኛዬ፡፡"መቶ ብር አበድረኝ" እለዋለው
ድፍኑን ነው ታድያ ይሰጠኛል እሷን እይዝና አንዷ ኮማሪት ቤት እገባለሁ "ስጪኝ" እላታለሁ "እሺ"
ትልና ትሰጠኛለች ተኝተን ስናበቃ ድፍን መቶ ብሩን እሰጣታለሁ፡፡ የእንትን ዋጋ እኮ አንድ ብር ነው፡፡
"ዝርዝር የለህም?"
ትለኛለች፡፡ ከፈለግሽ ዘርዝሪው እላታለሁ፡፡
"በቃ ነገ ስትመጣ ትሰጠኛለህ
ሂድ"
ትለኛለች ሌላ ቤት እገባለሁ ተመሳሳይ ዘዴ እጠቀማለሁ
፡፡ በአንድ ምሽት ሶስት አራት ቤት ገብቼ እወጣለሁ፡፡ መቶ ብር እኮ የአንድ ባለስልጣን የወር ደሞዝ ነው እንዴት ያለ ወርቅ ዘመን
መሰላችሁ መጠጥ ብትፈልግ በቅምሻ ትጠግባለህ….፡፡ በመጨረሻ በዛኑ ምሽት መቶ ብሩን ለፈድሉ እመልሳለሁ፡፡" በትዝታ እሩሩቅ
ተጓዘ………፡፡
*
* *
ከውስጤ ልውጣ አልውጣ እያለ የሚተናነቀኝን የኪነ ጥበብ ዛር ሰክኖ
እንዳይ እፎይ ብዩ እንድተነፍስ በተለይ ስነ-ግጥም ስሞነጭር በርካታ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ፡፡ ማንበቡ፤መወያየቱ እንዳለ ሆኖ የደረጃዬን
ልክ ሚዛን ማወቁ ግን ተስኖኛል እርዳታ የምፈልግበት ወቅት ነው፡፡ ሰውየውን አንድ ጥያቄ ልጨምርለት፡፡
"ጋሽ ስብሃት"
"ለበይክ…….."
"ደራሲ መሆን እፈልጋለሁ ምን ትመክረኛለህ?"
ከት ብሎ ሳቀ ሳቁ ግን አይሰማም ……..
"በቃ ዝም ብለህ ጻፍ ጻፍ የተሰማህን፤ያየህውን፤ስለገርል
ፍሬንድህ ቁጣ፤ቀጥረሃት ስለጠፋህበት ሁኔታ፤ስለ ንጭንጭኗ ፤ሳቅና ፈገግታዋ፤ እንዲህ ስለ ዛሬ ውሎአችን ፤ ስለዚህች መልካም ልጅ
" ፡፡ እጁን ቀስሮ አለምን እያሳየኝ፡፡
" ጻፍ ጻፍ ጻፍ…….."፡፡
"ግጥም መጻፍ ይመቸኛል ነው ያልከኝ? በጣም ከባድ እኮ ነው፡፡ እንካማ……
አንድ ቲያስ አሌዮት የተባለ ፈላስፋ የተናገረውን ላቀብልህ "ማንም
ታማኝ ገጣሚ ስለጻፈው ግጥም ዘላቂ ጥቅም እርግጠኛነት ሊሰማው አይችልም፡፡ጊዜውን ያባከነውና ህይወቱን ያመሰቃቀለው ያለአንዳች ፋይዳ
ሊሆን ይችላል " ይላል፡፡ ስለዚህ ግጥም ሙያ
አይደለም እጣ ፈንታ ነው" ፡፡
አለና ትንሽ እንደማሰብ ብሎ………
"ግን ለዝና ብለህ አትጻፍ ሲፈልግ አይታተም ፤ ብር አያምጣ ዘነበ
፤እኔ፤ እሱ ፤ እሷ ካነበብን ይበቃል"፡፡ ጨረሰ፡፡
በትንሽዬ ኮዳ የሚወዳትን ነገር ይዟል ከጠበሏ
ፉት አለ፡፡
ዳንኤል ብእርና ወረቀት አስጠጋለት
"ምን ላድርገው?"
"ፈርምልኝ"
"ለምንድነው የምፈርምልህ?"
"አድናቂህ ስለሆንኩ ነው"
"እሺ… ካልህ የራስህ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ
ቀን ደግሞ ሌላ እንዳትለኝ"
አለና ብእርና ወረቀቱን ተቀብሎ የሆነ ነገር
ጻፈና ፈረመ ፡፡ እኔም ከዳንኤል ተቀበልኩና አነበብኩት፡፡
"ሁለትም ሶስትም ባላችሁበት እኔ እገኛለሁ፡፡"
እየሱስ…………..
ከስር ፊርማ ፡፡
እኔም አስጠጋሁለት
"ደራሲ እሆናለሁ ተብሎ ደራሲ አይኮንም
"
ፊርማ…….
ቅድም የሳቀበት ምክንያት አሁን ገባኝ……………..
* *
*
የቀኗ ጀንበር ማዘቅዘቅ ጀምራለች የማይደክመው ስብሃት የተጠየውን
መመለስ ቀጥሏል፡፡ እውነት ለመናገር ስብሃት ትምህርት ቤት ነው ትልቅ ቤተ-መጽሐፍት……. እየተገለጠ የሚነበብ ብዙ ተማርኩበት…….
ከሱ ጋር መዋል ሱስ ያሲዛል፡፡ ዘነበ ወላ "ልጅነትን" እየጻፈ ነበር በወቅቱ የደረሰበትን ምእራፍ
ለስብሃት ለአብ ያነብለታል ሰውየው ያዳምጣል፡፡
"ቆይ እስቲ ያሁኑን አረፍተ ነገር ድገምልኝ"
ደግሞ ያነብለታል ዘነበ፡፡
ልጅ ሆኖ ስለ አበበ በቂላ የሚያውቀውን የሚተርክበት ቦታ
ነው ቶኪዮ ላይ ስላስመዘገበው ገድል……………
"እዚ ጋር እቺን ቃል አውጣት ይሄን ቃል
አስገባው"
ያርመዋል………
ዘነበ የተባለውን ይፈጽማል፡፡ አንድ ነገር ግን አልረሳም ከእጁ የማይጠፋውን
መቅረጸ ድምጽ ወደ ስብሃት አስጠግቶ ይቀርጻል አምስት የቴፕ ካሴቶች እፍራሹ ላይ ይታዩኛል ስድስተኛው መቅረጸ ድምጹ ውስጥ ተጠምዷል
፡፡
በዚህ መልኩ የተጠራቀመ የስብሃት ለአብ ልሳን ወደ ሰላሳ ካሴቶች ደረሱ
፡፡ ለጥቆ ዘነበ ላይ አንድ ነገር አጫረ ወደ መጽሃፍ መቀየር………..፡፡ ህልሙን እውን ለማድረግ ብዙ ጣረ አዎ በወረቀት መገልበጥ
ጀመረና 345 ገጥ ላይ ደረሰ እናም ብዙ የደከመው ዘነበ በ ወርሀ መጋቢት 1993 ዓም ተሳካለት እና የስበአት ለአብ "ማስታወሻ"
ተወለደ………….፡፡ እናም ስበሃትን አነበብነው ተዝናናንበት፤በፍቅሩ የወደቅን ውስጣችን እንዲገባ ፈቀድንለት፡፡ አዎ በርካታ ጸሃፍት
እግሩን፤ዱካውን ተከተሉ…….ስለ ነጭ ጢሙ፤ከእጁ ስለ ማትለየው ተአምረኛ ፌስታል፤ትከሻው ላይ ጣል ስለ `ሚያደርጋት ሹራብ ፤ ስለ
ንግግሩ ቃላት አጣጣሉ፤ዘገምተኛ አረማመድ(አካሄዱ)፤ስለ በላው ምግብ ስለ ጠጣው ነገር፤ስለ ነካው ስለ ጣለው ነገር ወዘተ……..
በተለያዩ ጊዜ በሚጽፏቸው መጣጥፎች፤ወጎች፤ረጅም ልብ-ወለዶች ማጣፈጫ ቅመም ሆነ…… መሪ ገጸ-ባሕሪ አድርገው ተጠቀሙበት ቆይ እንደውም
ከማስታውሰው የበአሉ ግርማ (ደራሲው) ፤የአዳም ረታ (እቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ) ሌላም ሌላም መጽሃፎች ውስጥ ታገኙታላቹ ፡፡ ወደፊትም
እንደሚጽፉት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሰዓሊያንስ ብትሉ ከጀማሪ እስከ አዋቂ የስብሃትን ገጽ (ትልልቅ ዓይኖቹን ያላፈጠጠ) ፤ (ነጭ
ጢሙን ያላንዠረገገ) ያልሞነጨረ ፊት ለፊት እያየው በሃሳብ ያላወራ………..ማን
አለ?፡፡ እኔም ሚስጥር ላውጣ በምችለው በተሰማኝ መንገድ በግጥም እፎፎፎፎፎይ ብያለሁ ፡፡
ስብሃት ለአብ
መሆን እንደሚፈልገው ሆኖ ፤ መጻፍ እንደሚፈልገው ጽፎ የሚኖር ደራሲ ነው፡፡ ነጻነቱ እጅግ ያስቀናኛል፡፡ ስንታችን ነን መሆን እንደምንፈልገው
ሆነን፤ ማድረግ የፈለግነውን አድርገን፤የኖርን? በአጉል ወግና ስርአት ተሸብበን፤በአጉል ባህልና ስርአት ተወጥረን መሆን ያለብንን
ሳንሆን አርቴፊሻል ኑሮ የተፈረደብን? በቤታችን በጉያችን ስንት ጉድ እና አመል ተሸክመን አደባባይ ለመታየት ፤ ለመምሰል የተሰለፍን?፡፡
እናም ከጋሽ ስብሃት ጋር ስትሆን መንፈስህ ይረጋጋል ክብድ ያለው ህይወትህ ቀለል ይልልሀል መኖር ማለት አሁን… ዛሬ… መሆኑን ትረዳለህ
እናም ከጋሽ ስብሀት ጋር ስሆን መንፈሳዊ ቅናት ያድርበኛል፡፡
የቀኑ ውሎአችን ሊገባደድ ነው መሽቷል፡፡ አንድ ጥያቄ ግን
ይቀረኛል፡፡
"ጋሽ ስብሀት"
"ለበይክ"
"አንተ ኮ ታዋቂ ደራሲ ነህ ለምንድ ነው የግል መኪና የሌለህ?"
አንገቱን
አቀርቅሮ ለትንሽ ደቂቃ ቆየ
"ምን አገባህ"
" እንዳልልህ አሳዘንከኝ ጥያቄህ የዋህነት ይነበብበታል ግን
እንካ ልንገርህ…… ከንቲባና ደራሲ በእግሩ ነው መሄድ ያለበት፡፡ በህዝብ መሃል መሹለክለክ፤ትንፋሹን መተንፈስ፤ለቅሶውን ማልቀስ፤ሲያስነጥሰው፤ማንጠስ
ደስታውን፤መደሰት ወዘተ…..፡፡ እነሱን እየጻፍኩ እነሱን እየኖርኩ ጉሮሮዬን እደፍናለው ከንቲባም ስለነሱ እያወራ ይሰነብታል ሁለታችንንም
እሚያኖረን ህዝብ ነው፡፡ ታድያ ይሄን ማግኘት የምትችለው በእግርህ ስትሄድ ነው፡፡ አንተን፤እናንተንስ በእግሬ ባልሄድ አገኛቹ ነበር
? " ጨረሰ፡፡
*
* *
ሰው ጊዜን ያህል ነገር እንዴት ይረሳል?፡፡ ያውም በልቡ
ውስጥ ገብቶ መላው ሰውነቱን ካናወዘው የአንድ ቀን አጋጣሚው እንዴትስ ሊዘነጋው ይችላል?፡፡ እንደው የእህል ውሃ ነገር ሆኖ ውሉን
በሳተ ጎዳና ከመክሊቱ ርቆ እሱነቱን አሳልፎ በመስጠት ኑሮን በመግፋት ሲኖር……ሁሌ መብሰክሰኩ፤መቃተቱ አንድ ቀን መዘመሩ፤እህህ
ማለቱ የተለመደ ነው፡፡
ከምኖርበት ከተማ ለስራ ጉዳይ ወደ አዱ ገነት መጥቻለሁ……ረጂም ጊዜ
ሆነኝ ከመጣሁ፡፡ ወደ ቦሌ ሽቅብ እየወጣን ነው ደንበል ህንጻ ጋር ስንደርስ ትራፊክ መበራት ያዘን በመስኮት አጮልቄ ግርግሩን እያየሁ
ነው ፡፡ ድንገት አንድ ሰው ላይ አይኔ ተተክሎ ቀረ አልተሳሳትኩም
ስብሃት ገብረ እግዚአብሄር ነው፡፡ ከአስራ ሶስት አመት በኋላ……፡፡ አላመንኩም ሰውየው እንዳለ ነው ፌስታሏም አለች……. ሹራቧም
ትከሻው ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ማመን አቃተኝ ከሱ እኔ አርጅቻለሁ መንፈሱ ጠንካራ ነው አረማመዱም እንደተጠበቀ፡፡ በትዝታ ወደኋላ
ተጓዝኩ………በአካል አይቼው አላውቅም ስለ ጤንነቱ ግን አልፎ አልፎ ከዘኔ ጋር እናወራለን በስልክ… ሲለው ደግሞ ካለሁበት ይመጣል
ወሬ ያቀብለኛል መታመሙን፤ሆስፒታል አስገብቶት እንደመጣ ነገረኝ አዘንኩ፡፡ መልካሙን እንዲገጥመው ተመኝተንም ተለያየን፡፡
ሰኞን አልወዳትም ፈረንጆቹም (black Monday) እያሉ ነው
የሚጠሯት፡፡ስራ ለመግባት በግድ ነው የተነሳሁት፡፡ ድንገት ተንቀሳቃሽ ስልኬ ጮኅች፡፡ ዘነበ ነው እንደፈራሁት ዜና እረፍቱን አረዳኝ፡፡
እናም እንዲህ ሲል ጨመረልኝ……………..
"አንድ ሙሉ ቤተ-መጽሀፍት ተቃጠለ"
እኔም እስማማለሁ ስብሃት ከዛም በላይ ነበር ብዙ ጸሀፍት
ብዙ እንደሚሉ እገምታለሁ ያልተባለ ያልተነገረለት ብዙ ነው እኔ አንድ ቀን አገኘሁት አንድ ቀን አወራሁለት ሺ ዘመን ግን እንዳነበው
ፍቀዱልኝ፡፡
* *
*
13/5/2004 ዓም
አደም ሁሴን
ናዝሬት
Adem_hussen@yahoo.com
Good, but try to say about his unspoken personality by using Ur critical lens. I think it makes Ur article full & unforgettable! Really I like Ur work!
ReplyDeleteAdem, You did great Job!! Thank you for sharing those beautiful memories. I wish i could be there, Alem invited me to attend, but i couldn't make it. Keep up.
ReplyDeleteዋው ለዚህ ጽሁፍ አጨብጭቤልሃለሁ።ጋሽ ስብሐት የሰጠህ ምክር ለእኔም የሰጠኝን ያህል ሆኖ ነው የተሰማኝ።እግዚአብሄር ይስጥልኝ አደም።እርሱንም ነፍሱን ይማር
ReplyDeletewow i like it
ReplyDeleteየጋሽ ስብሀት ስራው ልክ በሂወት ሲኖር እንደነበረው አካላዊ ገፅታና መንፈሱ የሚያረጅ አይደለም፡፡
ReplyDeleteላንተም እድሜና ጤና፡፡
ReplyDeleteለኛም ሺ ዓመት እንድናነበዉ የፈቀድክ አንተ ነህ፡፡ ይሄው እኔስ ከዐመታት በኀላ ደግሜ አነበብኩት፡፡ የጋሽ ስብሀት ስራም እንደሰዉነቱ ገዕታ አያረጅም ብል፡፡ ዉይ ....... ብቻ ላንተም መልካም እድሜ፡፡
ReplyDeleteአጀብ!የጋሽ ስብሃትን ልዕልና አግዝፈህ ስላሳየህን በኔም በአንባቢወቹም ስም ላመሰግንህ እወዳለሁ🙏
ReplyDeleteጋሽ ስብሐት በምደር ብቻ ሳይሆን በሰማይም ላሉት መደሰቻ መዛናኛ እና መማራያ መሆኑ አይቀረም ነፍስ ይማር
ReplyDelete