300ደቂቃ
በጣና ሀይቅ
ከማለዳው 3ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡
የባህር ዳር ሰማይ በትንሽ በትንሹ እዚም እዛም በቋጠሩ ደመናዎች ተሸፍኗል…… ጣና ሀይቅ ላይ ነኝ፡፡ አባይ አቋርጦት የሚሄድበትን
ቦታ ለማየት፡፡ ከሩቅ ገዳማት ይታዩኛል ክብራን ገብርኤል፤እንጦስ እየሱስ፤ደብረ ማርያም፤በትረ ማርያም፤እንዲሁም ሌሎች 10 ገዳማት……..ወደ`ዛም
እንሄዳለን የልቤ ምት ፍጥነቱን ጨምሯል……. መደበቅ አልቻልኩም ፍርሃት ፍርሃት እያለኝ ነው፡፡ ከዛ በፊት ግን ባለ ጀልባው አስጎብኚያችን
አባይ ጣናን አቋርጦ የሚያልፍበትን ቦታ ማየት እንዳለብን በመጠቆም ሊያሳየን የጀልባዋን ሞተር ገመድ ሳብ ሲያደርገው አንዴ እንደማጓራት
ብላ መንደቅደቋን ቀጠለች……፡፡
በታንኳ ለሁለተኛ ጊዜ መሳፈሬ ነው አንድ ጊዜ አዋሳ ሀይቅ ላይ ቀዝፌያለሁ……..
እነሆ ዛሬ ደግሞ ጣና ሀይቅ ላይ እገኛለሁ……፡፡ ጀልባዋ የጣናን ሀይቅ መሃሉን ሰንጥቃ እየተጓዘች ነው፡፡ አንድ ሴት አምስት ወንድ
ጓደኛሞች እና ባለጀልባ አስጎብኚያችንን ጨምራ ይዛለች፡፡ሁሉም በየራሱ የሀሳብ ማዕበል ተንሳፈዋል አብዛኛዎቹ ለውሀ ላይ ጉዞ አዲስ
ናቸው፡፡ ድንገት አንዱ ጓደኛችን የነበረውን ጸጥታ የሚሰብር ጥያቄ አቀረበ፡፡
"ጎበዝ የአደጋ መከላከያ ጃኬት አልያዝንም እኮ ብንሰምጥስ
?"
ለሁላችንም የሚሆን ጥያቄ አቀረበ አይኑ ግን አስጎብኚያችን ላይ
ተተክሏል፡፡
"አዎ ልክ ነህ እንዴት አልያዝንም ሾፌር እንመለስ እንጂ
ምን ነካህ…….?"
ሁሉም ተጓዦች ተንጫጩበት፡፡ ስጋታቸው ልክ ነበር
ድንገት አደጋ ቢደርስስ? ውሀ ላይ መንሳፈፍ የሚችል ከመሃላችን እኔና አስጎብኚያችን ብቻ ነን….. ጥያቄው፤ስጋቱ ከዘገየ ነው የቀረበው
ይህ ሁሉ ሲሆን ጣና መሃሉ ላይ ደርሰናል ሰማይና ምድር የተጣበቀ በሚመሰል መልኩ መሬት አይታይም ርቃናለች……የጀልባዋ ቀዛፊ ሊያረጋጋን ሞከረ፡፡ "አይዟችሁ ችግር የለም ዛሬ እንደ አጋጣሚ ማዕበል አልተነሳም ስለዚህ በሰላም እንገባለን " አለ፡፡ በቅጡ የሰሙት አልመሰለኝም ሁሉም በየራሱ ሀይማኖት
መጸለይ ጀምሯል…….እኔም ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ……"ድንገት ነዳጅ ቢያልቅበትስ? የጀልባዋ ሞተር አልሰራ ቢልስ? ሌላ መቅዘፊያ
እንኳ አልያዘ……!ኧረ ከዚህስ ጉድ ያውጣን……."፡፡ አስጎብኚያችን
ሌላ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አደረገ ፡፡
"ይልቅስ
ጀልባዋ ሚዛንዋን እንድትጠብቅ ግማሾች በቀኝ በኩል ግማሾች በግራ በኩል እኩል ተከፈሉና ተቀመጡ" ፡፡ አለን
ትእዛዙን ለመፈጸም ከሁሉ የቀደሙት ሁለቱ ጥንድ ፍቅረኛሞች ናቸው፡፡
አንገቱ ስር ተወሽቃ አይን አይኑን ታየዋለች የፈራች መሰለኝ ግን ደግሞ አይደለም……." የህይወቴ ህይወት አንተ ነህ…….ላጣህ አልፈልግም ሞት እንኳ ቢመጣ….." የምትል መሰለኝ ፡፡ ጣና ሀይቅ ላይ አሶች ሲደንሱ ጎሮ ወሸባዬ እያሉ በደስታ
ሲዘሉ፤በንፋስ ታግዞ፤ ነፋሻ አየር አዝሎ ከሀይቁ የሚነሳው ማእበል ጋር ህብር ፈጥረው ደስታህን ሲያደምቁ የኔ ከምትላት፤ከምትወዳት፤ፍቅረኛህ
ጋር ገላህን እየዳበሰ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ሲያልፍ ምን ያህል መታደል ነው? ቃላት ይኖረው ይሆን…….? ፡፡ የንዋይ ደበበ ተወዳጅ
ዘፈን ድንገት ትዝ አለኝ (ማእበል ነው ማእበል ነው ፍቅሯ) የሚለው……ከልቤ ቀናሁባቸው፡፡ ይህን መልካም አጋጣሚ፤ታሪካዊ ቀንን
በምስል አስደግፎ ለማስቀረት አልቦዘኑም ……አንድ ጊዜ አንገቱ ስር ውሽቅ ብላ፤አንድ ጊዜ እጁን ከእጇ አቆላልፋ እየተሳሳሙ…..እዚም
እዛም ፎቶግራፍ ብልጭ ብልጭ ይላል ለጊዜውም ቢሆን ቅድም የነበረው ፍርሃት ቀንሷል….፡፡ የጀልባዋ ሾፌር አስጎንኚያችን ማብራሪያና
ማስጠንቀቂያ ንግግሩን አላቋረጠም፡፡ ቀጠለናም…….
"አሁነም ስጋት አይግባችሁ እነዛን እንኳ አታዩም ብቻቸውን
እቃ ይዘው ሲቀዝፉ ……!" አለና ራቅ ራቅ ብለው የማገዶ እንጨት በባህላዊ መንገድ በተሰሩ
ጀልባዎች ጭነው የሚቀዝፉትን ሰዎች አመላከተን ፡፡ እንደ አስጎብኚያችን ማብራሪያ ከሆነ የባህላዊ ጀልባዋ ስም/ደንገል/ ይባላል
የተሰራችው ከሃይቁ በሚገኝ ሳር እና ጨፈቃ ሲሆን ብዙ ጊዜ እንደምታገለግል እና ጠንካራ እንደሆነች አሳ በማጥመድ፤ የማገዶ እንጨትና
ቄጤማ ሳር እንደሚጭኑበት እና ጀልባዋን በመስራት የሚታወቁት ደግሞ የወይጦ ማህበረሰብ ባለሙያዎች እንደሆኑ አስረዳን……
"ማገዶ እንጨቱን ግን ከየት ነው የሚያመጡት?"
፡፡ የኔ ጥያቄ ነበር
" እንጨቱን ሳሩን የሚጭኑት ደሴቱ ላይ ካሉት ገዳማት ነው በብዛት ግን የሚያመጡት ከመሀል ዘጌ ጊዮርጊስ ነው ምክንያቱም
ትንሽ ራቅ ስለሚልና ደሴቱም ሰፊ ስለሆነ በደንብ መልቀም ይችላሉ" አለን፡፡ አይኔ ቀዛፊዎቹ ላይ ተተክሎ እንደቀረ
ነው እውነትም ለጣና ሀይቅ ሌላው ጌጥ ናቸው፡፡ አሁን በቅርብ እርቀት እየታዩኝ ነው በፎቶ ምስላቸውን አስቀረሁ፡፡ በምላሹ ደስ
የሚል ኢትዮዽያዊ አክብሮት ያለው ሰላምታ ሰጡን ሙሉ በሙሉ ልብሳቸው በውሃ ርሷል…ምናልባት የሚንጠፈጠፍ ላብም ይሆናል፤ጭንቅላታቸው
በጨርቅ ተጠቅልሏል ያለማቋረጥ በሁለቱም በኩል ማንኪያ ቅርጽ ባለው እንጨት ውሀውን ያቀዝፋሉ……ሰማይ ላይ ተደርድረው አየሩን እንደ
ሚቀዝፉት አሞሮች መሰልኳቸው….፡፡ አይ ውሀ እና እንጀራ !!!!!፡፡
ጀልባዋ ጉዞዋን ቀጥላለች…..አስጎብኚያችን መረጃ መስጠት አላቋረጠም
" አሁን ወደ አባይ እየቀረብን ነው ከዛ በፊት ግን ትንሽ
ስለ ጣና ሀይቅ ልንገራችሁ……፡፡ እንደምታዩት ጣና ከባህር ዳር ከተማ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ በ3673 ስኩዌር ሜትር ስፋትና ከሰሜን
ደቡብ 75 ኪሎ ሜትር ከምስራቅ ምእራብ 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላይ ተንጣሎ ይገኛል፡፡ ጥልቀቱ በአማካኝ 9/ዘጠን/ ሜትር ነው
የጣና ሀይቅ በስፋቱ በሃገራችን ካሉ ታላላቅ ሀይቆች ቀዳሚ ሲሆን በአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዟል!፡፡ ሌላው ጣና ሀይቅ የሚያስደንቀው በውስጡ አስር የሚሆኑ ደሴቶች ይዟል በሙሉ
ገዳማት ናቸው ዳጋ እሲጢፋኖስ፤ኡራ ኪዳነምህረት፤ጣና ቂርቆስ፤ይጋንዳ ተ/ሀይማኖት፤አዝዋ ማርያም፤መሃል ዘጌ ጊዮርጊስ እንዲሁም ሌሎች……"፡፡ አለን፡፡ ማብራሪያው ድንቅ ነው……….
"ብራቮ ጣና ብራቮ ጣና"
ሳላስበው በስሜት ጮኩ…….፡፡ አሰጎበኚያችን
ትንሽ እንግሊዘኛ ቋንቋ እንደሚችልም አጫውቶኛል የውጪ ጎብኚዎች ሲመጡ ማስረዳትም እንደሚችል በኩራት ይናገራል ትምህርት ግን ብዙ
እንዳልገፋ እየተቆጨና እያዘነ ነገረኝ፡፡ አሁን ዓባይ ወንዝ ጋር ደረስን መሰለኝ የጀልባዋን ፍጥነት መቀነስ ጀመረ ቦታው ላይ ሲደርስም
ሞተሯን አጠፋት፡፡ "እሺ ወንድሞቼ አሁን ለመለየት ሞክሩ አባይ
ጣናን አቋርጦ የሚሄደው እዚህ ጋር ነው"፡፡ አለን..
ማንም ሊሞክረው አልቻለም ጀልባዋ በራሷ ሃይል መገፋት….. አቅጣጫ መቀየር ጀምራለች አዎ የዓባይ ወንዝ እያገዛት መሆን አለበት……!
ጠቆር ያለ የሆነ ቡኒ ቀለም አይነት ውሀ አዎ ትንሽ ያስቸግራል ግን አየሁት፤ለየሁት…. በኩራት ጣናን ሲያቋርጥ…… እንደ ዘንዶ
እየተጠማዘዘ እደ አንበሳ እተንጎማለለ……! ፡፡ ጸጥታው፤ዝምታው ያስፈራል "ስንት አመት በዚህ መልኩ ቀጠለ…..?"
ራሴን ጠየኩ ትኩር ብዬ እያየሁት ወደኋላ ረጅም ተጓዝኩ……ደቂቃዎች
እያለፉ ነው በያዝኩት ኮዳ ቀስ ብዬ ጨለፍኩት….. እናም ወደ ጉሮሮዬ አንቆረቆርኩት የሆነ የማላውቀው ስሜት ተሰማኝ ትኩስ አፈር
የሚጣፍጥ አፈር….ጨው..ጨው የሚል አፈር…….እንደገና የሆነ ስኳር ስኳር የሚል ስሜት……..እናም ሳላስበው ከውስጤ ፈነቀለኝ አለቀስኩ
ድምጽ አልባ ለቅሶ ወደውስጥ የሚሰርግ…… ለኔ ብቻ የሚሰማ ለቅሶ እንባዬ በጉንጩ ኮለል ብሎ አልፎ ዓባይን ተቀላቀለ ጠብ ጠብ ጠብ…..ወዴት
ይሆን መድረሻው?????........
* * *
ከገባሁበት ጥልቅ የስሜቴ ባህር መንጭቆ ያወጣኝ የጀልባዋ ሞተር
ድምጽ ነው፡፡ አሁን ጉዞ ወደ እንጦስ እየሱስ ገዳም ነው………፡፡
ይቀጥላል……..
Best article
ReplyDelete