Thursday, August 23, 2012

ያልተላከው ደብዳቤ


                        
ይህ ደብዳቤ ከ 15 ዓመት በፊት በቴሌቪዥን በመቶ ሃያ ፕሮግራም ላይ የፍቅር ደብዳቤ ውድድር ላይ ቀርቦ ተሸላሚ የሆነ ነው፡፡ ለትዝታ ይሆናችሁ ዘንድ ለጠፍኩት እንዲህም ደብዳቤ ይፃፍ ነበር እናነተስ የፍቅር ደብዳቤ ተፅፎላችሁ ወይ ፅፋችሁ ታውቃላችሁ?፡፡
                                                     Ø Ø Ø
       አሁን ልክ ከለሊቱ 9 ሰዓት አካባቢ ይመስለኛል……! መጥፎ ለሊት ዮሴፍ አንተ በዚህ ሰዓት ጥሩ እንቅልፍ ላይ እንደሆንክ አልጠራጠርም፡፡ በቃ እኔ ግን አልተኛሁም እንቅልፍን ከረሳሁ ሰነባበትኩ……! የምትናፍቀኝ አንተ ብቻ ነህ ድሮ እንኳን ያቺ ጨረቃ የኔ ትመስለኝ ነበር አሁን አሁን እሷም ርቃኛለች ሀሳቤን ሳልጨርስላት ትታኝ መግባት ጀምራለች፡፡ እናም ብቸኝነት መንፈሴን አብርዶታል የእኔ ውድ ግን ምን ያህል እንደማፈቅርህ ታውቅልኝ ይሆን……….?፡፡ ለህይወቴ ጥበቃ የምትሰጥልኝ ሰው መሆንህን አታውቀውም፤ አንድ ልብ አለን ስንል ለካስ የለንም እኔ ግን በሀሳቤ በፈጠርኩት ሐሳብ በመነሳት አንድ ሐሳብ አንድ ልብ ያለን ነበር የሚመስለኝ፡፡ ስርቅህ እስካይህ እቸኩላለሁ ሳገኝህ ደግሞ ቀና ብዬ እንኳን ለማየት ድፍረቱ የለኝም ፈራለሁ ፍቅር አንዳንዴ ፍረሀት ነው ልበል………….!?፡፡ ዮሴፍ ብዙ እለት ስለአንተ ያጫወትኳትን ጨረቃን ብትጠይቃት ትዘረግፍልሀለች፡፡ ያኔ ገና መፃፀፍ ስንጀምር ታስታውሳለህ……? “ ለሴት እንደኔ ምቹ የለም የሴት አንጀት ነው ያለኝ ሴትን እንደኔ ተንከባካቢም የለም ያልከኝን?፡፡ እኔ ግን እስከዛሬ አልረሳውም የምረሳውም አይመስለኝም ለሴት ልጅ የሚያዝን ሩህሩህ ቡቡ ልብ ያለው ወንድ ገና ከልጅነቴ ተቀርፆብኛል ዮሴፍ ነግሬህ የለ ጨካኝ ወንድ ያስፈራኛል፤ የኔ ውድ አስቴር አወቀን በይበልጥ የወደድኳት በየትኛው ዜማዋ እንደሆነ ታውቃለህ? “ሩህሩህ አዛኝ ነህ ልብል የማይጨክን ራስ ወዳድ ያልሆንክ ለሁሉ የምታዝን ” የሚለውን ሳዳምጥ ነው፡፡ በቃ አንተነትህ ይታየኛል በፊትህ እኮ ግርማ ሞገስ አለህ ገና ሳላይህ እንኳን ቡቡነትህ ሩህሩህነትህ ውስጤን ያተረማመሰው ነበር ዮሴፍ ዛሬማ ልሸሽግህ የምሻው ቅንጣት ነገር የለም ያኔ ስፅፍልህ ምነው አልነገርኩህም? በቃ ሰሰትኩህ ልበል ምናልባት የልቤን ብነግርህ እምትርቀኝ መስሎኝ ሰሰትኩህ፡፡ ደብዳቤህ ሲደርሰኝ ምን ያህል ውስጤ በደስታ እንደሚሞላ ያለኔና ያለ ፈጣሪ ማን ያውቃል ሰው እኮ ያለ ሀሳቡ አይራመድም እንጂ እኔማ ሀሳቤ ጥልቅ ነበር ንፁህ ነበር……..! ጓደኝነታችን የተቃና መልክ ይዞ በአንድ ወቅት ስለአንተ ብቻ ለመንገር ያለምኩት ምስጢር ነው አሁን እምፈታልህ ፡፡ አዎን የኔ ውድ ያለግዜው መንገር ግዴታዬ ሆነ ስለዚህም አድምጠኝ ለአንድ ዓመት ያህል በብዕር ጓደኝነት ቆየን……! እናም ለመገናኘት ቀጠሮ ያዝን በመጀመርያ ሳይህ የወደድኩት ምንህን እንደሆነ ታውቃለህ? ሩህሩህነትን ፊትህ ላይ ለማግኘት ተስገበገብኩ አገኘሁት ግን ሁለመናህ አዛኝነትህን ይመሰክራል ቀናቶች ገፉ በውስጤ እንደያዝኩህ እኔም ቀን ገፋሁ በቀጠሮ መገናኘቱ መጫወቱ በተለይ ደግሞ ስለጥበብ ብዙ መባባሉን ብናፍቀውም ከዚያ በላይ ደግሞ የውስጤ ሀሳብ ልውጣ አልውጣ እያለኝ ይታገለኝ ነበር አላወጣሁትም የኔ ውድ ትላንትና ግን ሁሉን ተረዳሁት በቃ በቅርቡ ጓደኛ እንደተዋወክ ነገርከኝ ላንተ ብስራት መስሎህ መንገርህ ነበር ለእኔ ግን ምፅአት ነው ውስጤ ተተረማመሰ ከዛሬ ከነገ ታውቅልኛለህ ብዬ ሳስብ ሌላ ሰው አወክ……! ግን በጣም ከፋኝ ሰው ሲከፋው አትወድም አይደል? ታዝናለህ ለእኔ ግን ብታዝንም ለውጥ ያለው አይመስለኝም፡፡          ቤት ገብቼ ላለቅስ ሞከርኩ የመከነ ለቅሶ ጨረቃም ያን ቀን አልነበረችም ዮሴፍ ላጣህ እንደማልሻ ልንገርህ አዎን በፍፁም ላጣህ አልፈልግም ባዶነት ይሰማኛል በኔ አስተያየት በኔ ባህሪ ሌላ ሰው መልመድ አይቻለኝም ግን ለካስ “ውሳኔ ማለት ህይወት ነው”፡፡ አዎን ብወስን ኖሮማ ይህ ሁሉ ባልሆነ እኔም ባልተንገላታሁ አንተንም ባላሳዘንኩህ ግን የኔ ሰው ዛሬም የኔ ውድ ብልህ ልክ ነኝ….? አውቀዋለሁ ግን ቢያንስ በልቤ እንድልህ ፍቀድልን፡፡ በቃ ብዙ አልጨቀጭቅህም አፈቅርህ እንደነበር ተረዳልኝ ከአንተም ሌላ በሐሳቤ ሊመጣ የሚችል ሰው ማንም የለም አሁንም አሁንም አልረሳህም፡፡ ዮሴፍ ልጅቷን ወደድካት? አዎን በጣም እንደምትወዳት አስባለሁ ደግሞም ውደዳት እዘንላትም ግን መውደድዋን በውስጧ አምቃ በስቃይ ለተንገላታችው ምስኪን ሰው ትንሽ እዘንላት በቃ ሌላ የምልህ የለኝም አልረሳህም ልተኛ ነው እንዲሁ ለመጋደም መንፈሴን ክፉኛ በርዶታል ግን መኖር ማለት ምንድነው? በቃ ግን እወድሀለሁ፡፡
                                            ያንተው-------

4 comments: