Wednesday, April 25, 2012

የሃይሌ ጽናት



ጀግናውን እንዴት እንዳገኘሁት !
       በወረሀ ሰኔ እሁድ ማለዳ 4ሰዓት ገደማ አዲስ አበባ ስቴድየም አካባቢ ዙርያ በዝግታ እየተራመድኩ ነው……..! ምክንያት ፡- በስቴድየም ዙርያ አንዳንድ የተዘጉ በሮች ጥግ ጥላ ተከልለው መጽሀፍ የሚሸጡ መጽሀፍ ነጋዴዎችን ለመጎንኘት ነው፡፡ ድንገት በጥላ ፎቅ መቀመጫ በስተግራ በኩል ያለው የተመልካች መግቢያ በር ክፍት ሆኖ አየሁ ፡፡ ምን ሊኖር ይችላል ብዩ ዘው ብዩ ገባሁ…….ማንም የጠየቀኝ የለም የኳስ ሜዳ ሳሩ ላይ….ግማሾች በመሮጫው ሜዳው ላይ በህብረት በህብረት ሆነው ሴቶች ለብቻ ወንዶች ለብቻ እሩጫ የሚሰለጥኑ አትሌቶች ተመለከትኩ…፡፡ሁሉም አረንጓዴ ቢጫ ቀይ ቀለም ያለው ቱታ ለብሰው ደምቀዋል……! ፡፤ እንዴት ደስ ይላል፡፡ እነማን እነንደሆኑ ለመለየት ያዳግታል፡፡ ድንገት እንደኔው አጥር ተደግፎ የታደመውን ልጅ እግር  ጠየኩት፡፡
# ወንድም የማን ቡድን ሯጮች ናቸው ? ; አልኩት እጁን ነካ አድርጌ
# ብሄራዊ ቡድን ናቸዋ ! አታውቃቸውም እንዴ ? ; መልሶ ጠየቀኝ …… ባውቅማ ለምን እጠይቀዋለሁ ? መልሼ ጠየኩት፡፡
# በናትህ ዕረ አላወኩም ታድያ ብሄራዊ ቡድን ከሆነ እዚህ ውስጥ ሃይሌ ገ/ስላሴ ፤ደራርቱ ቱሉ ይኖሩ ይሆን? ;አልኩት በጉጉት ልቤ በደስታ ልትቆም ደርሳለች
# አዎ አሉ…! እንደውም ያውልህ ከፊት ከሚሮጠው አትሌት ጀርባ የሚከተለው እሱ ነው እ እ እ……. ያቻትልህ ደራርቱ ግንባሯ ላይ ነጭ ጨርቅ ያሰረችው አሁን እንደውም ሳሩ ላይ ቁጭ ያለችው ; አለኝ፡፡ አይኔን ማመን ነው ያቃተው…..! ዓለምን ጉድ ያሰኘ ስመጥር ጀግና አትሌት በቅርብ ርቀት በዓይኔ በብረቱ እያየሁት ነው…..! ደስታ ፤ ፍርሃት…. የሆነ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት ተሰማኝ ! ፡፡ በቴሌቪዥን መስኮት ሃገሩን ወክሎ አለም አቀፍ ሩጫ ሲሮጥ ልቤ አብሮት ሮጧል…….ተፎካካሪን ጥሎ ሲገባ ! ፤በደስታ ባንዲራ ለብሶ ሲጨፍር ! በደስታ አልቅሻለሁ፡፡ የኔ የወንዜ የሃሀሬ ልጅ በመሆኑ ኮርቻለሁ ፡፡ ዓለም ዝቅ ዝቅ ያደረጋትን ፤የናቃትን የሀገሬን ባንዲራ ከፍ ብሎ እንዲሰቀል ፤ እንዲውለበለብ አድርጓል ……ሀይሌ ለሃገሩ ደምቷል….! ቆስሏል …….! ከዚህ በላይ ማለት አልችልም የተባለ ለመድገም ካልሆነ  በስተቀር….፡፡
    # ሄጄ ማነጋገር አለብኝ….. ግን ደግሞ ምን ብዩ ? እንዴትስ ሆኖ ? ማንስ ያስጠጋኛል ?;
ራሴን ጠየኩ…. መልስ የለም…… አይኔ ጀግናው ላይ ተተክሎ ቀርቷል ስቴድየሙን እየዞሩ ነው አሁንም ሀይሌ ከኋላ ነው የሚከተለው …..የሴቶቹ ቡድን ሩጫቸውን ጨርሰው ደራርቱ ከተቀመጠችበት ቦታ ላይ ተሰብስበው ተቀመጡ ሁሉም ፊት ላይ በድካም ውስጥ ፈገግታ ይነበባል ይሳሳቃሉ አንዷ ከአንዷ ትከሻ ላይ ተደጋግፈው፤አንገት ለአንገት ተቃቅፈው  ሳይ አንድነታቸው ፍቅራቸው አስቀናኝ…….! የወንዶቹ ቡድን የሩጫ ስልጠናው አላለቀም ፡፡ አሰልጣኝ ዶ/ር ወልደመስቀል ኮስትሬ ደረታቸው ላይ ያንጠለጠሉትን ትልቅ ሰዓት እየተቆጣጠሩ ፍጥነት እንዲጨምሩ በእጃቸው ምልክት ይሰጣሉ…….አሁን ሀይሌ ፍጥነት ጨመረ እንደ ሰጎን እየተምዘገዘገ እንደ አንበሳ እያገሳ፤እንደ አቦ ሸማኔ እየተለመጠ  ሌሎችን እየሳበ ይሮጣል……..ድንገት በሚስማር ተራ መታጠፊያ መአዘን ላይ ሲደርስ ግን እግሩን ማነከስ ጀመረ ብዙም አልቆየ ከሯጮቹ ተነጥሎ በዝግታ እየተራመደ ሜዳ ላይ ከነበረው ነጭ ፕላስቲክ ወንበር ላይ ተቀመጠ ……፡፡ አሁን ነው ሰዓቱ አልኩኝ በሆዴ ሄጄ ማነጋገር አለብኝ በቃ ወድሃለሁ ! ፤አከብርሃለሁ ! ፤አንተ የኛ ጌጥ ነህ ! ፤ ጀግና ነህ ! ልለው ይገባል አልኩ በስሜት…….፡፡
                            ©   ©   ©
          ስቴድየም ውስጥ ዙረያውን ወንፊት በሚመስል የሽቦ አጥር ታጥሯል ወደ ውስጥ ዘልቆ መግባት አይቻልም …ጨነቀኝ ፡፡ ዘዴውን ያውቅ እንደሆነ ከጎኔ ያለውን ልጅ አሁንም አስቸገርኩት፡፡
# ወንድም ወደ ውስጥ እንዴት ነው ሚገባው ? ሃይሌን ማግኘት ማነጋገር እፈልጋለሁ …..! ; አልኩት አይን አይኑን እያየሁ፡፤
# መግባት ትፈልጋለህ ? እንግዲህ ከቀናህ ይኅውልህ ፖሊሱ የቆመበት ቦታ ወደ ውስጥ የሚያስገባ በር ነው ጠባቂውን ለምነው….. ከፈቀደልህ ትገባለህ በል ይቅናህ ; አለኝ፡፡ በስተቀኝ በኩል ያለውን የመግቢያ በር እየጠቆመኝ ፡፡ ስለትብብሩ አመሰገንኩት… የጠቆመኝ መግቢያ ግን ፈጽሞ በር አይመስልም ተመመሳሳይ የሽቦ አጥር ነው ፡፡ እየተጠጋሁ በመጣሁ ቁጥር ግን ክፍቱን ያለ ያልተቆለፈ በር አየሁ…ፖሊሱ አሁንም እዛው ነው፡፡ ልለምነው አለምነው ከራሴ ሙግት ገጥሜ ደቂቃዎች አለፉ፡፡ ድንገት ከአጥሩ ውጪ ሙሉ ቱታ የለበሰ ሰው የአጥሩን በር ከፍቶ ሲገባ ተከትየው ገባሁ…ፖሊሱ አልጠየቀኝም ከሰውየው ጋር ይሆናል ብሎ እንዳሰበ ገመትኩ ሀይሌ አሁንም ወንበሩ ላይ ተቀምጧል በጣም እየቀረብኩት ነው ፡፡ ወጌሻው ቀኝ እግሩ ታፋ ላይ ፋሻ ጠቅልሎለት ስራውን ጨርሶ ሄዷል…….፡፡ አሁን እኔና ጀግናው ሀይሌ የአንድ እርምጃ ልዩነት ነው ያለን አላየኝም ፊቱ በላብ ተጠምቋል ግንባሩ ላይ በትንሽ በትንሹ የተቋጠሩ የላብ እንክብሎች ይታዩኛል ፡፡ ጀግንነቱን አይበገሬነቱን አይቶ ብቻ መመስከር ይቻላል ልቤ ከኔ ጋር መኖር አለመኖርዋን ለማረጋገጥ እጄን ወደ ደረቴ አስጠጋሁ…..!
 #ጤና ይስጥልኝ ሃይሌ……; አልኩት ያለኝን ሀይል ፤ ጉልበት ሁሉ አጠራቅሜ ቀና ብሎ አየኝ ፡፡ በድካሙ ውስጥ ፈገግታው አለ………………
# ጤና ይስጥልኝ ደህና ነኝ ; አለና እጁን ዘርግቶ ጨበጠኝ ፡፡ እጁ በጣም ይለሰልሳል ጥንካሬው ግን እንዳለ ነው ማመን አቃተኝ በህልም የሆነ ያህል ነው የተሰማኝ ፡፡
# በጣም አድናቂህ ነኝ ሃይሌ ዛሬ አንተን በማግኘቴ ትልቅ እድለኛ እንደሆንኩ ነው የምቆጥረው ; አልኩት፡፡
# እሺ በጣም ነው የማመሰግነው ፡፡ የአዲስአበባ ልጅ ነህ ? ; አለኝ፡፡
# አይ አይደለሁም የክፍለ ሃገር ልጅ ነኝ ;
# ታስታውቃለህ ጥርስህ ይናገራል ! ; አለኝ ፍሎራይድ ያበላሸውን ጥርሴን መቅላት እየተመለከተ ፡፡ በስምጥ ሸለቆ ውስጥ የሚኖር ሰው ከውሃው ከሚመጣ በሙሉ የዚህ ችግር ተጋላጭ ነው፡፡
# የናዝሬት ልጅ ነህ ? ;
# እዛው አካባቢ ነኝ ብዙም አልርቅም ; አልኩት…….፡፡ ጊዜ ሰጥቶ እያወራኝ መሆኑ ደስ ብሎኛል ከዚህ በላይ ምን እጠይቀዋለሁ…. ጀግናው አንገቱን አቀርቅሮ የግራ ታፋው ላይ የተጠቀለለውን እግሩን እያሻሸ ፤ እየነካካ ነው የህመም ስሜት እየተሰማው መሆኑ ፊቱ ላይ ያስታውቃል
#ሀይሌ ምን አጋጥሞህ ነው ?; አልኩት፡፡
# ትንሽ የጡንቻ መሸማቀቅ ነው ለክፉ አይሰጥም ከባድ ልምምድ ስላደረኩበት ነው ይተወኛል ; አለኝ ፡፡ ፈጣሪን ለመንኩለት እንዲሻለው ፡፡
በቃ #እወድሃለሁ; አልኩትና ብዕርና ወረቀት አስጠጋሁለት
# እዚች ጋር ፈርምልኝ ; አልኩት፡፡
# እሺ ምን ችግር አለ ; አለና ስሙን ጽፎ ፈረመልኝ፡፡ ከዚ በላይ መቆየት አልቻልኩም የወንድ ሯጮቹ ቡድንም ሩጫውን ጨርሰው ሀይሌ ወደተቀመጠበት ቦታ እየመጡ ነው፡፡ ለስንብት እጄን ዘረጋሁለት በምላሹ በፍቅር ጨበጠኝ…….! የዚህን ጀግና ፍቅር ! ፤ ስሜት አይበገሬነት ! ፤ ስምና ፊርማውን የያዘ ወረቀት ይ¹ ወደ ቤቴ ገሰገስኩ፡፡ በጥንቃቄ ፎቶ አልበሜ ውስጥ ፊርማውን ማህተብ አኖርኩ……፡፡ ይኅው እስከዛሬ በማስታወሻ የያዝኩት ፊርማ አብሮኝ አለ ፡፡ የዛኑ ቀን አመሻሽ ላይ ለሱ ያለኝን ፍቅርና አድናቆት በግጥም ጽፌ አስቀመጥኩ፡፡
                          ©    ©    ©
       ጀግናው ሻለቃ ኀይሌ ገ/ስላሴን ከዛን ጊዜ ወዲህ በአካል አይቼው ፤ አግኝቼው አላውቅም…የጻፍኩትን ግጥም ማስታወሻ ትሆነው ዘንድ ልሰጠው አስቀምጨ ድፍን አስራ ሶስት ዓመት አስቆረ……. ፡፡ እነሆ ዛሬ ከቆለፉኩበት ሳጥን ውስጥ አውጥቼ አየር ላይ እንድለቀው ያደረገኝ ምክንያት በቅርቡ በኤሌክትሮኒክስ መረጃ መረብ አንድ አስተያየት ሰጪ ስለሃይሌ ከሰይፉ ፋንታሁን (ጋዜጠኛ) ጋር ባደረገው ቃለ ምልልስና ቃለ ምልልሱን ተከትሎ፤-   ኃይሌ የወርቃማው እግሮችህ ውለታ በምላስህ እንዳይደበዝዙ ! በሚል ርዕስ ስር የተሰጠ አስተያየት (የአስተያየት ሰጪውን መብት ባከብርም) እኔ ግን ያልተዋጠልኝና በተለይ ከትልልቅ ሰዎች ጋር የሚደረግ ቃለ ምልልስ ጠያቂው ወይም ጋዜጠኛው ስለ ተጠያቂው ስለ ሚጠይቀው ጉዳይ በቂ እውቀት እንዳለው የማወቅ ሃላፊነት ያለበት ይመስለኛል…… የሚጠየቀውም ተጠያቂ ከሚጠየቀው ርዕስ ጋር ተዛማጅነት እውቀት መኖሩን ሳያረጋግጥ በሚሰጥ መልስ የሚያስከትለው መዘዝ በተለይ በታዋቂ ሰዎች የከፋ ነው ፡፡ ዞሮ ዞሮ በዚህ ጉዳይ ወደፊት እመለስበታለሁ::
   ሃይሌ ግን ዛሬም እግሩም ልቡም ለሀገሩ እንደሚሮጥ ግን ተስፋ አደርጋለሁ……
እውን ሀይሌ ሀይህችን ግጥም ትደርሰው፤ያነበው  ይሆን ??!! ፡፡


Tuesday, April 24, 2012

የምሽት ፈርጥ


ጠረኔን መልሱ

ይህችን ግጥም ስጽፋት ወደ ደቡብ አርባ ምንጭ ለመዝናናት ሄጄ ነው፡፡ ወዳጆቼ ከአድማስ ማዶ ከተሰደዱበት ሃገር ሲመለሱ መጀመርያ የሚያገኙት እኔን ነው፡፡
# አቦ ወጣ እንበል ; እላቸዋለሁ
# እሺ አንተ እንዳልክ ; ይሉኛል… ፕሮግራሙን እናቅዳለን ፡፡ ረዘም ያለ ጉዞ ይመቸኛል ! ተፈጥሮን እየኮመኮሙ ንጹህ አየር እየሳቡ ፤ እየቀዘፉ መጓዝ መጓዝ………! ፡፡
ቀኑ የገበያ ቀን ነው አርባ ምንጭ ላይ…… ከዋናው የከተማዋ አደባባይ በስተ ገራ አንድ ፎቅ ያላት ቆንጆ ኬክ ቤት አለች ማለዳ ላይ ተሰብስበን ቡና እየጠጣን ነው የሃመር ኮረዶች በአጠገባችን እያለፉ አየሁ
# እንዴ ከየት ነው የመጡት ?; አለ አንዱ ዲያስፖራ ጓደኛችን……. እውነቱን ነው ወደ ሃመር ቱርሚ ለመሄድ ቀጠሮ ይዘናል ! እነሆ እነሱ ቀደሙንና አየናቸው…………፡፡
ገበያ ሲሆን አንድ አንድ ጊዜ ብቅ እንደሚሉ ተነገረን በከተሜው ሰው……!
ድንገት አንዷ የሃመር ወጣት ላይ አይኔ ተተክሎ ቀረ……….! ልብ የሚሰልብ ውበት አላት……! ፡፡ እናም ብእሬን ከወረቀት አዋደድኩ፡፡
© © ©
ማስታወሻነቷ ለነ እንትና ነው፡፡ ልድገመው ለነ ( እ….ን…..ት….ና ! )

300ደቂቃ በጣና ሀይቅ


300ደቂቃ በጣና ሀይቅ
                ከማለዳው 3ሰዓት አካባቢ ይሆናል፡፡ የባህር ዳር ሰማይ በትንሽ በትንሹ እዚም እዛም በቋጠሩ ደመናዎች ተሸፍኗል…… ጣና ሀይቅ ላይ ነኝ፡፡ አባይ አቋርጦት የሚሄድበትን ቦታ ለማየት፡፡ ከሩቅ ገዳማት ይታዩኛል ክብራን ገብርኤል፤እንጦስ እየሱስ፤ደብረ ማርያም፤በትረ ማርያም፤እንዲሁም ሌሎች 10 ገዳማት……..ወደ`ዛም እንሄዳለን የልቤ ምት ፍጥነቱን ጨምሯል……. መደበቅ አልቻልኩም ፍርሃት ፍርሃት እያለኝ ነው፡፡ ከዛ በፊት ግን ባለ ጀልባው አስጎብኚያችን አባይ ጣናን አቋርጦ የሚያልፍበትን ቦታ ማየት እንዳለብን በመጠቆም ሊያሳየን የጀልባዋን ሞተር ገመድ ሳብ ሲያደርገው አንዴ እንደማጓራት ብላ መንደቅደቋን ቀጠለች……፡፡
           በታንኳ ለሁለተኛ ጊዜ መሳፈሬ ነው አንድ ጊዜ አዋሳ ሀይቅ ላይ ቀዝፌያለሁ…….. እነሆ ዛሬ ደግሞ ጣና ሀይቅ ላይ እገኛለሁ……፡፡ ጀልባዋ የጣናን ሀይቅ መሃሉን ሰንጥቃ እየተጓዘች ነው፡፡ አንድ ሴት አምስት ወንድ ጓደኛሞች እና ባለጀልባ አስጎብኚያችንን ጨምራ ይዛለች፡፡ሁሉም በየራሱ የሀሳብ ማዕበል ተንሳፈዋል አብዛኛዎቹ ለውሀ ላይ ጉዞ አዲስ ናቸው፡፡ ድንገት አንዱ ጓደኛችን የነበረውን ጸጥታ የሚሰብር ጥያቄ አቀረበ፡፡
         "ጎበዝ የአደጋ መከላከያ ጃኬት አልያዝንም እኮ ብንሰምጥስ ?"
          ለሁላችንም የሚሆን ጥያቄ አቀረበ አይኑ ግን አስጎብኚያችን ላይ ተተክሏል፡፡
         "አዎ ልክ ነህ እንዴት አልያዝንም ሾፌር እንመለስ እንጂ ምን ነካህ…….?"
ሁሉም ተጓዦች ተንጫጩበት፡፡ ስጋታቸው ልክ ነበር ድንገት አደጋ ቢደርስስ? ውሀ ላይ መንሳፈፍ የሚችል ከመሃላችን እኔና አስጎብኚያችን ብቻ ነን….. ጥያቄው፤ስጋቱ ከዘገየ ነው የቀረበው ይህ ሁሉ ሲሆን ጣና መሃሉ ላይ ደርሰናል ሰማይና ምድር የተጣበቀ በሚመሰል መልኩ መሬት አይታይም ርቃናለች……የጀልባዋ  ቀዛፊ ሊያረጋጋን ሞከረ፡፡ "አይዟችሁ ችግር የለም ዛሬ እንደ አጋጣሚ ማዕበል አልተነሳም ስለዚህ በሰላም እንገባለን " አለ፡፡ በቅጡ የሰሙት አልመሰለኝም ሁሉም በየራሱ ሀይማኖት መጸለይ ጀምሯል…….እኔም ለራሴ ጥያቄ አቀረብኩ……"ድንገት ነዳጅ ቢያልቅበትስ? የጀልባዋ ሞተር አልሰራ ቢልስ? ሌላ መቅዘፊያ እንኳ አልያዘ……!ኧረ ከዚህስ ጉድ ያውጣን……."፡፡ አስጎብኚያችን ሌላ ማስጠንቀቂያ አዘል ንግግር አደረገ ፡፡
       "ይልቅስ ጀልባዋ ሚዛንዋን እንድትጠብቅ ግማሾች በቀኝ በኩል ግማሾች በግራ በኩል እኩል ተከፈሉና ተቀመጡ" ፡፡ አለን
      ትእዛዙን ለመፈጸም ከሁሉ የቀደሙት ሁለቱ ጥንድ ፍቅረኛሞች ናቸው፡፡ አንገቱ ስር ተወሽቃ አይን አይኑን ታየዋለች የፈራች መሰለኝ ግን ደግሞ አይደለም……." የህይወቴ ህይወት አንተ ነህ…….ላጣህ አልፈልግም ሞት እንኳ ቢመጣ….." የምትል መሰለኝ ፡፡ ጣና ሀይቅ ላይ አሶች ሲደንሱ ጎሮ ወሸባዬ እያሉ በደስታ ሲዘሉ፤በንፋስ ታግዞ፤ ነፋሻ አየር አዝሎ ከሀይቁ የሚነሳው ማእበል ጋር ህብር ፈጥረው ደስታህን ሲያደምቁ የኔ ከምትላት፤ከምትወዳት፤ፍቅረኛህ ጋር ገላህን እየዳበሰ የማይረሳ ትዝታ ጥሎ ሲያልፍ ምን ያህል መታደል ነው? ቃላት ይኖረው ይሆን…….? ፡፡ የንዋይ ደበበ ተወዳጅ ዘፈን ድንገት ትዝ አለኝ (ማእበል ነው ማእበል ነው ፍቅሯ) የሚለው……ከልቤ ቀናሁባቸው፡፡ ይህን መልካም አጋጣሚ፤ታሪካዊ ቀንን በምስል አስደግፎ ለማስቀረት አልቦዘኑም ……አንድ ጊዜ አንገቱ ስር ውሽቅ ብላ፤አንድ ጊዜ እጁን ከእጇ አቆላልፋ እየተሳሳሙ…..እዚም እዛም ፎቶግራፍ ብልጭ ብልጭ ይላል ለጊዜውም ቢሆን ቅድም የነበረው ፍርሃት ቀንሷል….፡፡ የጀልባዋ ሾፌር አስጎንኚያችን ማብራሪያና ማስጠንቀቂያ ንግግሩን አላቋረጠም፡፡ ቀጠለናም…….
          "አሁነም ስጋት አይግባችሁ እነዛን እንኳ አታዩም ብቻቸውን እቃ ይዘው ሲቀዝፉ ……!" አለና ራቅ ራቅ ብለው የማገዶ እንጨት በባህላዊ መንገድ በተሰሩ ጀልባዎች ጭነው የሚቀዝፉትን ሰዎች አመላከተን ፡፡ እንደ አስጎብኚያችን ማብራሪያ ከሆነ የባህላዊ ጀልባዋ ስም/ደንገል/ ይባላል የተሰራችው ከሃይቁ በሚገኝ ሳር እና ጨፈቃ ሲሆን ብዙ ጊዜ እንደምታገለግል እና ጠንካራ እንደሆነች አሳ በማጥመድ፤ የማገዶ እንጨትና ቄጤማ ሳር እንደሚጭኑበት እና ጀልባዋን በመስራት የሚታወቁት ደግሞ የወይጦ ማህበረሰብ ባለሙያዎች እንደሆኑ አስረዳን……
               "ማገዶ እንጨቱን ግን ከየት ነው የሚያመጡት?" ፡፡ የኔ ጥያቄ ነበር
          " እንጨቱን ሳሩን የሚጭኑት ደሴቱ ላይ ካሉት ገዳማት ነው በብዛት ግን የሚያመጡት ከመሀል ዘጌ ጊዮርጊስ ነው ምክንያቱም ትንሽ ራቅ ስለሚልና ደሴቱም ሰፊ ስለሆነ በደንብ መልቀም ይችላሉ" አለን፡፡ አይኔ ቀዛፊዎቹ ላይ ተተክሎ እንደቀረ ነው እውነትም ለጣና ሀይቅ ሌላው ጌጥ ናቸው፡፡ አሁን በቅርብ እርቀት እየታዩኝ ነው በፎቶ ምስላቸውን አስቀረሁ፡፡ በምላሹ ደስ የሚል ኢትዮዽያዊ አክብሮት ያለው ሰላምታ ሰጡን ሙሉ በሙሉ ልብሳቸው በውሃ ርሷል…ምናልባት የሚንጠፈጠፍ ላብም ይሆናል፤ጭንቅላታቸው በጨርቅ ተጠቅልሏል ያለማቋረጥ በሁለቱም በኩል ማንኪያ ቅርጽ ባለው እንጨት ውሀውን ያቀዝፋሉ……ሰማይ ላይ ተደርድረው አየሩን እንደ ሚቀዝፉት አሞሮች መሰልኳቸው….፡፡ አይ ውሀ እና እንጀራ !!!!!፡፡
          ጀልባዋ ጉዞዋን ቀጥላለች…..አስጎብኚያችን መረጃ መስጠት አላቋረጠም " አሁን ወደ አባይ እየቀረብን ነው ከዛ በፊት ግን ትንሽ ስለ ጣና ሀይቅ ልንገራችሁ……፡፡ እንደምታዩት ጣና ከባህር ዳር ከተማ ሰሜናዊ ጫፍ ላይ በ3673 ስኩዌር ሜትር ስፋትና ከሰሜን ደቡብ 75 ኪሎ ሜትር ከምስራቅ ምእራብ 60 ኪሎ ሜትር ርዝመት ላይ ተንጣሎ ይገኛል፡፡ ጥልቀቱ በአማካኝ 9/ዘጠን/ ሜትር ነው የጣና ሀይቅ በስፋቱ በሃገራችን ካሉ ታላላቅ ሀይቆች ቀዳሚ ሲሆን በአፍሪካ 3ኛ ደረጃን ይዟል!፡፡ ሌላው ጣና ሀይቅ የሚያስደንቀው በውስጡ አስር የሚሆኑ ደሴቶች ይዟል በሙሉ ገዳማት ናቸው ዳጋ እሲጢፋኖስ፤ኡራ ኪዳነምህረት፤ጣና ቂርቆስ፤ይጋንዳ ተ/ሀይማኖት፤አዝዋ ማርያም፤መሃል ዘጌ ጊዮርጊስ እንዲሁም ሌሎች……"፡፡ አለን፡፡ ማብራሪያው ድንቅ ነው……….
                      "ብራቮ ጣና ብራቮ ጣና"
ሳላስበው በስሜት ጮኩ…….፡፡ አሰጎበኚያችን ትንሽ እንግሊዘኛ ቋንቋ እንደሚችልም አጫውቶኛል የውጪ ጎብኚዎች ሲመጡ ማስረዳትም እንደሚችል በኩራት ይናገራል ትምህርት ግን ብዙ እንዳልገፋ እየተቆጨና እያዘነ ነገረኝ፡፡ አሁን ዓባይ ወንዝ ጋር ደረስን መሰለኝ የጀልባዋን ፍጥነት መቀነስ ጀመረ ቦታው ላይ ሲደርስም ሞተሯን አጠፋት፡፡ "እሺ ወንድሞቼ አሁን ለመለየት ሞክሩ አባይ ጣናን አቋርጦ የሚሄደው እዚህ ጋር ነው"፡፡ አለን.. ማንም ሊሞክረው አልቻለም ጀልባዋ በራሷ ሃይል መገፋት….. አቅጣጫ መቀየር ጀምራለች አዎ የዓባይ ወንዝ እያገዛት መሆን አለበት……! ጠቆር ያለ የሆነ ቡኒ ቀለም አይነት ውሀ አዎ ትንሽ ያስቸግራል ግን አየሁት፤ለየሁት…. በኩራት ጣናን ሲያቋርጥ…… እንደ ዘንዶ እየተጠማዘዘ እደ አንበሳ እተንጎማለለ……! ፡፡ ጸጥታው፤ዝምታው ያስፈራል "ስንት አመት በዚህ መልኩ ቀጠለ…..?" ራሴን ጠየኩ ትኩር ብዬ እያየሁት  ወደኋላ ረጅም ተጓዝኩ……ደቂቃዎች እያለፉ ነው በያዝኩት ኮዳ ቀስ ብዬ ጨለፍኩት….. እናም ወደ ጉሮሮዬ አንቆረቆርኩት የሆነ የማላውቀው ስሜት ተሰማኝ ትኩስ አፈር የሚጣፍጥ አፈር….ጨው..ጨው የሚል አፈር…….እንደገና የሆነ ስኳር ስኳር የሚል ስሜት……..እናም ሳላስበው ከውስጤ ፈነቀለኝ አለቀስኩ ድምጽ አልባ ለቅሶ ወደውስጥ የሚሰርግ…… ለኔ ብቻ የሚሰማ ለቅሶ እንባዬ በጉንጩ ኮለል ብሎ አልፎ ዓባይን ተቀላቀለ ጠብ ጠብ ጠብ…..ወዴት ይሆን መድረሻው?????........
                                *   *   *
           ከገባሁበት ጥልቅ የስሜቴ ባህር መንጭቆ ያወጣኝ የጀልባዋ ሞተር ድምጽ ነው፡፡ አሁን ጉዞ ወደ እንጦስ እየሱስ ገዳም ነው………፡፡
ይቀጥላል……..






ሌቱም አይነጋልኝ


,,,,እነሆ በረከት ወ ስበሃት ,,,,,,,
         አስራ አራት ዓመት ወደኋላ ልመልሳችሁ ነው……. ጨርቆስ አካባቢ አንዲት ውብ ጓደኛችን ቤት ታድመናል ሁላችንም አንድ አይነት ፍላጎት ፤አንድ አይነት አስተሳሰብ እና ለኪነ-ጥነብ ልዩ ፍቀር ያለን ጓደኞች፡፡ አንድ ትልቅ እንግዳ ልንቀበል ነው፡፡ ነገሩ ምን መቀበል ብቻ ምናልባት ስለሱ ተሰምቶ፤ተወርቶ የማያልቀውን ዝናውን እውቀቱን ህይወቱን ብቻ ሁሉ ነገሩን ለመቋደስ፡፡ ቤቷ ጠባብ ነች ግን ትበቃናለች፡፡ ቆይ ስንት ነን ዳንኤል፤ ዳዊት፤አለም፤ እኔ…….. ማ ቀረ? እንግዳው ጋሽ ስብሃት እንግዳውን ይዞት የሚመጣው ጋዜጠኛና ደራሲ ዘነበ ወላ፡፡
      አዎ በህይወቴ እጅግ ደስ ያለኝ ቀን ቢኖር ስብሃትን የዛን ቀን በአካል ያገኘሁት እለት ነው፡፡ሁሉ ነገር ተዘጋጅቷል፡፡ ምሳ ፓስታ ነው የተጋበዘው ደስታው ወደር አልነበረውም፡፡
ምግብ ሰሪዋን ምን ብሎ እንዳመሰገናት ልንገራችሁ፡፡ "አለም" ጠራት ፡፡ "እኔና ቤቴ ግን አግዚያብሄርን እናመሰግናለን"፡፡
ሁላችንም የቻልነውን፤ውስጣችን የሚመላለሰውን ነገሮች ሁሉ መጠየቅ ጀመርን ሰውየው ይመልሳል……….
                 "እስቲ ስለ ኤሚ ዞላ አጫውተን"
     ዳዊት ነው ጠያቂው ስለፈረንሳዊው ታዋቂ ደራሲ በደስታ ይመልሳል የደራሲውን ግልጽነት፤ደፋርነት አነጋጋሪነት የቃላት አመራረጥ ዘዴውን…….. እኔም ቀጠልኩ
                       "ጋሽ ስበሃት"
                             "ለበይክ" አለኝ
              "ስለ ቼኮቬራ አውርተህ አትጨርስም  ለኔም ብታካፍለኝ" ፡፡ ጠየኩት፡፡                                                
              ድንገት ከተቀመጠበት ፍራሽ ላይ ብድግ ብሎ ቆመ፡፡
    " ጥሩ ጥያቄ ነው ቼኮቬራን ግን ቁጭ ብዬ አይደለም የማወራልህ አጥንቱ ይወጋኛል"
       አለና "ቼ..ለኔ ልዩ ሰው ነው መልዓክ አይነት…. ግን ቆይ ሃኪም እንደነበር የሚያውቅ ሰው አለ ከመሃላችሁ?" ጠየቀን….. መልስ የለም፡፡ የሚመስጥ ታሪኩን አውርቶ ሲጨርስ እ….እፎይ ብሎ ተቀመጠ፡፡ መልሶ እኔን ጠየቀኝ
                         "አንተ ግን ሙስሊም ነህ ?"
                               "አዎ ነኝ"
                          "ቁርአን አንብበሃል?"
                             "አላነበብኩም"
                       "ቀረብህ ኢቅራ….." አለኝ፡፡
     እሱ ኮ…ቁርአንን ፉት አደርጎ አንብቦታል ማንበብ ብቻ ሳይሆን የእስልምናን አመጣጥ የነብዩ መሀመድን፤ገድል፤ስርአት፤አስተምሮት፤ጠንቅቆ እንደሚያውቅ፤ እንደሚወደው፤ ታሪኩ እንደሚመስጠው አጫወተኝ ተገረምኩ፡፡ ዳንኤል ሰለሰ………
 "ጋሽ ስበሃት"
                                 "አቤት ወዳጄ"
                  "ስለ ውበት ያለህን አመለካከት እባክህ ጀባ በለኝ"
         "መረሃባ ዳኒ ቆይ የሴት ጡት ጫፉን ትኩር ብለህ አይተህ ታውቃለህ?"
                               "ኧ…..ረ አላውቅም"
     ደነገጠ …. እኔም ደንግጫለሁ…. ሁላችንም ፊታችንን ወደ ቤቷ ባለቤት ጓደኛችን አለም አዞርን ሴት እሷ ብቻ ነች……..ጋሽ ስብሃት ግን አልገረመውም ፤አልደነቀውም ፤ አልደነገጠም ፡፡ ቀጠለ…..
 "በቃ ውበት ማለት በተወጠረ የሴት ጡት ጫፍ ላይ የምታየውን አይበገሬነት ይመስላል "
    ነጻነቱ ገረመኝ በወሬ የሰማሁትን በአይኔ አየሁት፡፡ አንድ ጥያቄ መጠየቅም ፈለኩ
                               "ጋሽ ስበሃት"
                                 "ለበይክ"
    "ለበይክ" ማለት ( አቤት) እንደማለት ነው በአረብኛ፡፡
                     "አንድ ጥያቄ ልጠይቅህ ነው"
                                 "ማለፊያ ጠይቃ"
       "ብዙ ጊዜ ስለ ውቤ በረሃ አንስተህ አትጠግብም ደግሞ ወቤ በረሃን እንደወረደ ማውራት፤ማንሳት ትወዳለህ ምንድነው ሚስጥሩ?"፡፡ አልኩት መልሱን እየጓጓሁ፡፡
                       "መርሃባ ና እጅህን አምጣ"
          አለኝና የመጨረሻ ጣቱን ቀስሮ ሌሎቹን አጥፎ ወደኔ ዘረጋቸው፡፡እኔም እሱ እንዳደረገው ተከተልኩት፡፡ የመጨረሻ ጣቶቻችንን እንዳቆላለፍን ከሰኮንዶች ቆይታ በኋላ አላቀን ሳም አደረግናቸው እንደልጅነታችን……
            "አሁን የምወደውን ጥያቄ ጠየክ ይኅውልህ ውቤ በረሃ ለኔ ገነት እንደማለት ነው፡፡ የዋህነትን ፤ቀጥተኛነትን ፤የምታውቅበት የሚገባህ ዘመን ነው፡፡ ያኔ ደንሰህ፤ጨፍረህ፤ሀጢያትህን አስነጥሰህ የምትመለስበት ቦታ ፡፡ ብር የለም ያኔ የፈለከውን ግን ታገኛለህ መደነስ ካማረህ ደንሰህ፤መጠጣት ካማረህ ጠጥተህ፤ሴት ማቀፍ ካማረ አቅፈህ ትመለሳለህ በነጻ፡፡ እኔማ በዚህ እታወቃለሁ፡፡ መንግስት የሚከፍለኝ ብር አይበቃኝማ ታድያ እሞታለሁ ፡፡ አንድ ባለ ሱቅ ነበር..ቆይ ስሙ ጠፋኝ እንዴ……? አዎ ፈድሉ ይባላል ባለ ሱቅ ነው ደንበኛዬ፡፡"መቶ ብር አበድረኝ" እለዋለው ድፍኑን ነው ታድያ ይሰጠኛል እሷን እይዝና አንዷ ኮማሪት ቤት እገባለሁ "ስጪኝ" እላታለሁ "እሺ" ትልና ትሰጠኛለች ተኝተን ስናበቃ ድፍን መቶ ብሩን እሰጣታለሁ፡፡ የእንትን ዋጋ እኮ አንድ ብር ነው፡፡
                                 "ዝርዝር የለህም?"
                          ትለኛለች፡፡ ከፈለግሽ ዘርዝሪው እላታለሁ፡፡
                          "በቃ ነገ ስትመጣ ትሰጠኛለህ ሂድ"
ትለኛለች ሌላ ቤት እገባለሁ ተመሳሳይ ዘዴ እጠቀማለሁ ፡፡ በአንድ ምሽት ሶስት አራት ቤት ገብቼ እወጣለሁ፡፡ መቶ ብር እኮ የአንድ ባለስልጣን የወር ደሞዝ ነው እንዴት ያለ ወርቅ ዘመን መሰላችሁ መጠጥ ብትፈልግ በቅምሻ ትጠግባለህ….፡፡ በመጨረሻ በዛኑ ምሽት መቶ ብሩን ለፈድሉ እመልሳለሁ፡፡" በትዝታ እሩሩቅ ተጓዘ………፡፡
                       *     *     *
         ከውስጤ ልውጣ አልውጣ እያለ የሚተናነቀኝን የኪነ ጥበብ ዛር ሰክኖ እንዳይ እፎይ ብዩ እንድተነፍስ በተለይ ስነ-ግጥም ስሞነጭር በርካታ ጊዜያትን አሳልፌያለሁ፡፡ ማንበቡ፤መወያየቱ እንዳለ ሆኖ የደረጃዬን ልክ ሚዛን ማወቁ ግን ተስኖኛል እርዳታ የምፈልግበት ወቅት ነው፡፡ ሰውየውን አንድ ጥያቄ ልጨምርለት፡፡
                              "ጋሽ ስብሃት"
                                "ለበይክ…….."
                  "ደራሲ መሆን እፈልጋለሁ ምን ትመክረኛለህ?"
            ከት ብሎ ሳቀ ሳቁ ግን አይሰማም ……..
                "በቃ ዝም ብለህ ጻፍ ጻፍ የተሰማህን፤ያየህውን፤ስለገርል ፍሬንድህ ቁጣ፤ቀጥረሃት ስለጠፋህበት ሁኔታ፤ስለ ንጭንጭኗ ፤ሳቅና ፈገግታዋ፤ እንዲህ ስለ ዛሬ ውሎአችን ፤ ስለዚህች መልካም ልጅ " ፡፡ እጁን ቀስሮ አለምን  እያሳየኝ፡፡
                      " ጻፍ ጻፍ ጻፍ…….."፡፡
          "ግጥም መጻፍ ይመቸኛል ነው ያልከኝ? በጣም ከባድ እኮ ነው፡፡ እንካማ…… አንድ ቲያስ አሌዮት የተባለ ፈላስፋ የተናገረውን ላቀብልህ "ማንም ታማኝ ገጣሚ ስለጻፈው ግጥም ዘላቂ ጥቅም እርግጠኛነት ሊሰማው አይችልም፡፡ጊዜውን ያባከነውና ህይወቱን ያመሰቃቀለው ያለአንዳች ፋይዳ ሊሆን ይችላል " ይላል፡፡ ስለዚህ ግጥም ሙያ አይደለም እጣ ፈንታ ነው" ፡፡
        አለና ትንሽ እንደማሰብ ብሎ………
    "ግን ለዝና ብለህ አትጻፍ ሲፈልግ አይታተም ፤ ብር አያምጣ ዘነበ ፤እኔ፤ እሱ ፤ እሷ ካነበብን ይበቃል"፡፡ ጨረሰ፡፡
                   በትንሽዬ ኮዳ የሚወዳትን ነገር ይዟል ከጠበሏ ፉት አለ፡፡
                        ዳንኤል ብእርና ወረቀት አስጠጋለት
                                 "ምን ላድርገው?"
                                  "ፈርምልኝ"
                           "ለምንድነው የምፈርምልህ?"
                             "አድናቂህ ስለሆንኩ ነው"
                  "እሺ… ካልህ የራስህ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላ ቀን ደግሞ ሌላ እንዳትለኝ"
አለና ብእርና ወረቀቱን ተቀብሎ የሆነ ነገር ጻፈና ፈረመ ፡፡ እኔም ከዳንኤል ተቀበልኩና አነበብኩት፡፡
                     "ሁለትም ሶስትም ባላችሁበት እኔ እገኛለሁ፡፡"
                                     እየሱስ…………..
                                                ከስር ፊርማ ፡፡
                                        እኔም አስጠጋሁለት
                       "ደራሲ እሆናለሁ ተብሎ ደራሲ አይኮንም "
                                                 ፊርማ…….
                            ቅድም  የሳቀበት ምክንያት አሁን ገባኝ……………..

                                *      *        *
             የቀኗ ጀንበር ማዘቅዘቅ ጀምራለች የማይደክመው ስብሃት የተጠየውን መመለስ ቀጥሏል፡፡ እውነት ለመናገር ስብሃት ትምህርት ቤት ነው ትልቅ ቤተ-መጽሐፍት……. እየተገለጠ የሚነበብ ብዙ ተማርኩበት……. ከሱ ጋር መዋል ሱስ ያሲዛል፡፡ ዘነበ ወላ "ልጅነትን" እየጻፈ ነበር በወቅቱ የደረሰበትን ምእራፍ ለስብሃት ለአብ ያነብለታል ሰውየው ያዳምጣል፡፡
                    "ቆይ እስቲ ያሁኑን አረፍተ ነገር ድገምልኝ"
ደግሞ ያነብለታል ዘነበ፡፡
ልጅ ሆኖ ስለ አበበ በቂላ የሚያውቀውን የሚተርክበት ቦታ ነው ቶኪዮ ላይ ስላስመዘገበው ገድል……………
                  "እዚ ጋር እቺን ቃል አውጣት ይሄን ቃል አስገባው"
       ያርመዋል………
 ዘነበ የተባለውን ይፈጽማል፡፡ አንድ ነገር ግን አልረሳም ከእጁ የማይጠፋውን መቅረጸ ድምጽ ወደ ስብሃት አስጠግቶ ይቀርጻል አምስት የቴፕ ካሴቶች እፍራሹ ላይ ይታዩኛል ስድስተኛው መቅረጸ ድምጹ ውስጥ ተጠምዷል ፡፡
           በዚህ መልኩ የተጠራቀመ የስብሃት ለአብ ልሳን ወደ ሰላሳ ካሴቶች ደረሱ ፡፡ ለጥቆ ዘነበ ላይ አንድ ነገር አጫረ ወደ መጽሃፍ መቀየር………..፡፡ ህልሙን እውን ለማድረግ ብዙ ጣረ አዎ በወረቀት መገልበጥ ጀመረና 345 ገጥ ላይ ደረሰ እናም ብዙ የደከመው ዘነበ በ ወርሀ መጋቢት 1993 ዓም ተሳካለት እና የስበአት ለአብ "ማስታወሻ" ተወለደ………….፡፡ እናም ስበሃትን አነበብነው ተዝናናንበት፤በፍቅሩ የወደቅን ውስጣችን እንዲገባ ፈቀድንለት፡፡ አዎ በርካታ ጸሃፍት እግሩን፤ዱካውን ተከተሉ…….ስለ ነጭ ጢሙ፤ከእጁ ስለ ማትለየው ተአምረኛ ፌስታል፤ትከሻው ላይ ጣል ስለ `ሚያደርጋት ሹራብ ፤ ስለ ንግግሩ ቃላት አጣጣሉ፤ዘገምተኛ አረማመድ(አካሄዱ)፤ስለ በላው ምግብ ስለ ጠጣው ነገር፤ስለ ነካው ስለ ጣለው ነገር ወዘተ…….. በተለያዩ ጊዜ በሚጽፏቸው መጣጥፎች፤ወጎች፤ረጅም ልብ-ወለዶች ማጣፈጫ ቅመም ሆነ…… መሪ ገጸ-ባሕሪ አድርገው ተጠቀሙበት ቆይ እንደውም ከማስታውሰው የበአሉ ግርማ (ደራሲው) ፤የአዳም ረታ (እቴ ሜቴ የሎሚ ሽታ) ሌላም ሌላም መጽሃፎች ውስጥ ታገኙታላቹ ፡፡ ወደፊትም እንደሚጽፉት ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ሰዓሊያንስ ብትሉ ከጀማሪ እስከ አዋቂ የስብሃትን ገጽ (ትልልቅ ዓይኖቹን ያላፈጠጠ) ፤ (ነጭ ጢሙን ያላንዠረገገ) ያልሞነጨረ  ፊት ለፊት እያየው በሃሳብ ያላወራ………..ማን አለ?፡፡ እኔም ሚስጥር ላውጣ በምችለው በተሰማኝ መንገድ በግጥም እፎፎፎፎፎይ ብያለሁ ፡፡
            ስብሃት ለአብ መሆን እንደሚፈልገው ሆኖ ፤ መጻፍ እንደሚፈልገው ጽፎ የሚኖር ደራሲ ነው፡፡ ነጻነቱ እጅግ ያስቀናኛል፡፡ ስንታችን ነን መሆን እንደምንፈልገው ሆነን፤ ማድረግ የፈለግነውን አድርገን፤የኖርን? በአጉል ወግና ስርአት ተሸብበን፤በአጉል ባህልና ስርአት ተወጥረን መሆን ያለብንን ሳንሆን አርቴፊሻል ኑሮ የተፈረደብን? በቤታችን በጉያችን ስንት ጉድ እና አመል ተሸክመን አደባባይ ለመታየት ፤ ለመምሰል የተሰለፍን?፡፡ እናም ከጋሽ ስብሃት ጋር ስትሆን መንፈስህ ይረጋጋል ክብድ ያለው ህይወትህ ቀለል ይልልሀል መኖር ማለት አሁን… ዛሬ… መሆኑን ትረዳለህ እናም ከጋሽ ስብሀት ጋር ስሆን መንፈሳዊ ቅናት ያድርበኛል፡፡
            የቀኑ ውሎአችን ሊገባደድ ነው መሽቷል፡፡ አንድ ጥያቄ ግን ይቀረኛል፡፡
                                "ጋሽ ስብሀት"
                                   "ለበይክ"
             "አንተ ኮ ታዋቂ ደራሲ ነህ ለምንድ ነው የግል መኪና የሌለህ?"
                   አንገቱን አቀርቅሮ ለትንሽ ደቂቃ ቆየ
                                "ምን አገባህ"
       " እንዳልልህ አሳዘንከኝ ጥያቄህ የዋህነት ይነበብበታል ግን እንካ ልንገርህ…… ከንቲባና ደራሲ በእግሩ ነው መሄድ ያለበት፡፡ በህዝብ መሃል መሹለክለክ፤ትንፋሹን መተንፈስ፤ለቅሶውን ማልቀስ፤ሲያስነጥሰው፤ማንጠስ ደስታውን፤መደሰት ወዘተ…..፡፡ እነሱን እየጻፍኩ እነሱን እየኖርኩ ጉሮሮዬን እደፍናለው ከንቲባም ስለነሱ እያወራ ይሰነብታል ሁለታችንንም እሚያኖረን ህዝብ ነው፡፡ ታድያ ይሄን ማግኘት የምትችለው በእግርህ ስትሄድ ነው፡፡ አንተን፤እናንተንስ በእግሬ ባልሄድ አገኛቹ ነበር ? " ጨረሰ፡፡
                      *        *        *
             ሰው ጊዜን ያህል ነገር እንዴት ይረሳል?፡፡ ያውም በልቡ ውስጥ ገብቶ መላው ሰውነቱን ካናወዘው የአንድ ቀን አጋጣሚው እንዴትስ ሊዘነጋው ይችላል?፡፡ እንደው የእህል ውሃ ነገር ሆኖ ውሉን በሳተ ጎዳና ከመክሊቱ ርቆ እሱነቱን አሳልፎ በመስጠት ኑሮን በመግፋት ሲኖር……ሁሌ መብሰክሰኩ፤መቃተቱ አንድ ቀን መዘመሩ፤እህህ ማለቱ የተለመደ ነው፡፡
             ከምኖርበት ከተማ ለስራ ጉዳይ ወደ አዱ ገነት መጥቻለሁ……ረጂም ጊዜ ሆነኝ ከመጣሁ፡፡ ወደ ቦሌ ሽቅብ እየወጣን ነው ደንበል ህንጻ ጋር ስንደርስ ትራፊክ መበራት ያዘን በመስኮት አጮልቄ ግርግሩን እያየሁ ነው ፡፡ ድንገት አንድ ሰው ላይ  አይኔ ተተክሎ ቀረ አልተሳሳትኩም ስብሃት ገብረ እግዚአብሄር ነው፡፡ ከአስራ ሶስት አመት በኋላ……፡፡ አላመንኩም ሰውየው እንዳለ ነው ፌስታሏም አለች……. ሹራቧም ትከሻው ላይ ተንጠልጥሏል፡፡ ማመን አቃተኝ ከሱ እኔ አርጅቻለሁ መንፈሱ ጠንካራ ነው አረማመዱም እንደተጠበቀ፡፡ በትዝታ ወደኋላ ተጓዝኩ………በአካል አይቼው አላውቅም ስለ ጤንነቱ ግን አልፎ አልፎ ከዘኔ ጋር እናወራለን በስልክ… ሲለው ደግሞ ካለሁበት ይመጣል ወሬ ያቀብለኛል መታመሙን፤ሆስፒታል አስገብቶት እንደመጣ ነገረኝ አዘንኩ፡፡ መልካሙን እንዲገጥመው ተመኝተንም ተለያየን፡፡
          ሰኞን አልወዳትም ፈረንጆቹም (black Monday) እያሉ ነው የሚጠሯት፡፡ስራ ለመግባት በግድ ነው የተነሳሁት፡፡ ድንገት ተንቀሳቃሽ ስልኬ ጮኅች፡፡ ዘነበ ነው እንደፈራሁት ዜና እረፍቱን አረዳኝ፡፡ እናም እንዲህ ሲል ጨመረልኝ……………..
                    "አንድ ሙሉ ቤተ-መጽሀፍት ተቃጠለ"
              እኔም እስማማለሁ ስብሃት ከዛም በላይ ነበር ብዙ ጸሀፍት ብዙ እንደሚሉ እገምታለሁ ያልተባለ ያልተነገረለት ብዙ ነው እኔ አንድ ቀን አገኘሁት አንድ ቀን አወራሁለት ሺ ዘመን ግን እንዳነበው ፍቀዱልኝ፡፡
                 *       *       *
                                   13/5/2004 ዓም
                                     አደም ሁሴን
                                         ናዝሬት
                                               Adem_hussen@yahoo.com

ነገር የገባት ቆቅ


መጓዝ ለኔ ማወቅ ነው….በሄድንበት ወይም በተጓዝንበት ቦታ ሁሉ አዲስ ነገር ይገኘኛል አዲስ አየር፤አዲስ ሰው ፤አዲስ አስተሳሰብ ፤ወግ ባህል፤አዲስ ፍቅር አዲስ አዲስ አዲስ ነገር…….፡፡ መጓዝ ለኔ እንዲህ ነው፡፡ አንድ ስሙን የማላስታውሰው የሀገሬ ሰው #ሀበሻ የቆመበት ቦታ መቀበር ይችልበታል ; ይላል፡፡ እኔም እስማማለሁ…..በዚህች በትንሽ የህይወት ዘመኔ በርካታ ወዳጆች አፍርቻለሁ፡፡ ከምሁር እስከ ነጋዴ አቅም ያላቸው ሌሎች የማህበረሰብ ክፍሎች…..መብታቸው እንደጠጠበቀ ሆኖ ታሪክ ከማወቅ ተፈጠሮን ሀገርን ከማወቅ በዘለለ አንድ መጠጥ ግሮሰሪ ውስጥ ወይም ኮማሪት ቤት በርካታ አጫፋሪ በመሰብሰብ ወይም ወግ ደላቂ በማዋቀር ብርጭቆና ጠርሙስ እያጋቡ በሚረጩት ብር ጀግንነታቸው እንዲነገርላቸው እንዲወደሱ የሚፈልጉ ድንገት ስለታሪክ ስለሃገር ሲነሳ የሚያማቸው ወይም ሲጠየቁ ግራ የሚገባቸው ብዙ ወዳጆች አጋጥመውኛል፡፡ልድገመው (መብታቸው ግን እንደተጠበቀ ይቆይ) ነገር ግን ከዚህ መሃል ላይ መገኘት ግን ምን ያህል አለመታደል እንደሚሆን ገምቱልኝ……ጋዜጠኛና ደራሲ ነብይ መኮንን ( አዲስ አድማስ ) ጋዜጣ ሳገላብጥ እንዲህም የሚል አስነበበኝ፡፡
ኤልዳስ ሄክስ ሌይ የተባለ ታዋቂ ደራሲ እንዲህ ሲል መስክሯል (መጓዝ ማንም ሰው ስለሌሎች ሀገሮች መሳሳቱን ለማወቅ ይጠቅመዋል) ይለናል ፡፡ አቦ እኔም እስማማለሁ…… እንዲህ እንደማለት እኮ ነው….የሆነች ልጅ አይተሃት መስሪያ ቤት ወይም የሆነ ቦታ ሊሆን ይችላል ወይም በምተለብሰው አጭር ጉርድ ቀሚሷ ወይም ከንፈሯን በምትቀባው ቀይ ሊፒስቲክ ሰበብ ወይም ፍጥን ፍጥን በሚለው አነጋገርዋ የሆነ ስም ፈጥረህላት ቆይተሀል አንተ ጠልተሀት ሌላውንም አሳድመህ ሰንብተሀል…..ግን በአጋጣሚ ቀርበሀት፤ተግባብተሀት ያ…ሁሉ ግምትህና ልፋትህ መናሲቅብህ እንደማለት ነው፡፡እናም የነበረን ግምትና በአይን አይቶ የማረጋገጥ መሀል ያለውን ሰፊ ክፍተት ያስረዳናል፡፡ በዚህ አጋጣሚ ነብይ መኮንን ሳላደንቅ ሳላመሰግን ባልፍ ይቆጨኛል፡፡ በሄደበት ፡በተቀመጠበት ሁሉ ያየውን፤የሰማውን፤ያሸተተውን፤የቀመሰውን ጽፎ ያስነብበናል…ያወቀውን ያሳውቀናል……ጣትህ ይባረክ በየዋለሁ እኛም እንከተላለን፡፡ አሜን! ፡፡
ሀገሬን ጠቅልዪ የማየት ህልም አለኝ፡፡ ( ይሄ የሁላችሁም ምኞት እንደሚሆን አልጠራጠርም ) እንደ አጋጣሚ ሆኖ በርካታ ቦታዎችን ጎብኝቻለሁ፡፡ እሳት ከሚዘንብበት ከሚመስለው እትዩ-ጅቡቲ ጠረፍ ጋላፊ አንስቶ በአራቱም አቅጣጫ እዛም አዚም በትንሽ በትንሹ፡፡ መቼም ለኔ ነፍሴ ሀሴት የደስታ ጣራ ላይ የምትደርሰው ወደ ደቡብ ስጓዝ ነው……በቃ ልቤ ጮቤ ይረግጣል፡፡ ወድጄም አይለም ሀሳብና ጭንቄን በትክክል ሳጥን ውስጥ የሚቆለፉት ያኔ ነው ተመላልሼ ደጋግሜ አይቼዋለሁ የደቡብን መንገድ ስጀምር ሰላም አገኛለሁ…..ተፈጥሮን ለመቋደስ ፤ ለማጣጣም ብሎም ለኪነጥበብ ውስጥ ለመመላለስ በተመስጦ ለማሰብ ያመቻል ወይም ያመቸኛል……….ቆይ አንድ አጋጣሚ ላስታውሳችሁ፡፤ ታዋቂው ዘፋኝ ቴዎድሮስ ካሳሁን በአንድ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንዲህ ሲል የሰማሁት መስሎኛል፡፡(ጃ ያስተሰርያል ) የሚል ሀገር ያናወጠ ሃሪፍ ስራ ሰርቶ ነበር እናም እሱ ልብ ውስጥ ገብቼ ስሜቱን ባልናገርም ስራወን እንደ ጨረሰ ለሊቱን ሙሉ ወደ ሀዋሳ ሲነዳው እንዳደረና ደስታውንም ከሀዋሳና ከሃዋሳ ህዝብ ጋር እንዳሳለፈ ተናግሯል፡፡እኔም ልመስክር አጋጣሚ ሆኖ እዛ በነበርኩበት ወቅት ቴዲን አይቼዋለሁ እናም እነዛን ቱባ ስራዎች የሚፈጥረው አዋሳ ሀይቅ ዳር ሆኖ ይሆን እንዴ ? ብዪ ጠረጠርኩ፡፡

አሁን ሀዋሳ ደርሻለሁ፡፡ እዚህ ፍቅር አለ አሞራ ገደል ከዋርካው ጥላ ስር ትኩስ ፍቅረኛሞች ተካቅፈው ፍቅር ሲጎራረሱ ታያለህ ወፎች ይዘምራሉ የተለያየ ድምጽ ነው የሚያወጡት የሆነ ደስ የሚል ሽታ ደሞ አለ የአበባ፤የግራር ወዘተ…..ሀይቁ ላይ አሶች ሲደንሱ ፤አባ ኮዳ፤ጦጣ ፤ጉሬዛ እየተቀባበሉ ትርኢት ሲያሳዩ ትደመማለህ ታቦር ተራራ ከሩቁ ና ወዲህ ይልሃል ሀዋሳን ሊያስጎበኝህ የሜትር አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ታሪካዊ  ቪላ ቤትም እዛ ይገኛል ከዛ በላይ ደግሞ በዙ አርቲስቶች የሚጎበኙት የሚታደሙበት አንድ ቤት አለ ሙዚቀኛው፤ደራሲው፤ሰዓሊው፤የትያትር ባለሙያው ቤቷን ሳይሳለም አይመለስም፡፡ ምናልባት ባለቤቶቹ ለኪነ ጥበብ ቅርብ ስለሆኑ ብዩ ገምቻለሁ፡፡ መስተንግዶአቸው ልዩ ነው…እኔም ማረፊያዩ እዛው ነው፡፡ በርካታ አርቲስቶች ተሰብስበው አጋጠሙኝ ቀደም ብሎ የግቢው መናፈሻ ውስጥ የታየኝ ገለታ ነው አርቲስት ገለታ ተ/ጻዲቅ ደስ ከሚለው ጢሙ ጋር….በረንዳው ላይ አርቲስት ችሮታው ከልካይ፤ፋንቱ ማንዶዩ፤ጋጋ፤ፍልፍሉ ሌሎች በርካታ አርቲስቶች ይታዩኛል ተራ በተራ ተዋወኳቸው ደስታዩ ወደር አልነበረውም እንዴት ደስ ይላል ! ፎቶግራፍ ማንሳት ጀመርኩ……ድንገት ፋንቱ ማንዶዩ ጠራኝ
# ስማኝ ወንድም ላስቸግርህ ; አለኝ
# ãረ ችግር የለም ምን ልታዘዝ ; አልኩት
#ይኀውልህ እኔ ህጻን ልጅ ቶሎ አይቀርበኝም ፊቴ ያስፈራቸዋል፤ድምጼ ያስበረግጋቸዋል ይህችን ልጅ ግን ተመልከታት ገና ስጠራት ሮጣ መጣች አውቅሃለው አለቺን የምጠይቃትን ሁሉ በንቃት ትመልሳለች ልቧ የአርቲስት ነው ( ነገር የገባት ቆቅ ነች ) ; ፡፡ አለና ወደራሱ አስጠጋት
# በል ፎቶ አንሳኝ በጣም ነው የሚያስፈልገኝ ደግሞ መርቄያታለሁ አርቲሰት ሁኚ ብዩ ;
አለና ለፎቶ ተዘጋጀ እኔም አነሳሁት ደጋገምኩት ከዛን ጊዜ በኋላ ፋንቱ ማንዶዩን በአካል አግኝቼው አላውቅም አርቲስት ችሮታው ከልካይን ግን ትግራይ መቀሌ አገኘሁት አላመነም የመሃል ሀገር ሰው ሰሜን ጥግ ያውም ባልተገመተ ሁኔታ….፡፡ ቆንጆ ጊዜ አሳለፍን አንድ ዝግጅታቸውን ጋበዘኝ ማስታወሻ ፎቶ ተነስተን ተለያየን::
ይህች ነገር የገባት ቆቅ እድሜ ጨምራለች፤ጨዋታም እንዲሁ ፋንቱ ማንዶዩ ምን እንደቀባት አላውቅም ልጅቷ የምታሳየው ጥበብ የተለየ ነው የከርሞ ሰው ይበለንና እንጽፈዋለን !!::