Wednesday, January 16, 2013

ሀዋሳ ቤሌማ……!



ሀዋሳ ቤሌማ……!
1
              “መጓዝ ማወቅ ነው…..!” ፡፡ እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ1995 ዓም (ከአስር ዓመት በፊት መሆኑ ነው) በወርሃ መስከረም ላይ በአሁን ሰዓት ላይ የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ክልል በዋና ከተማነት የምታገለግለውን ሃዋሳ ከተማ ለመጀመርያ ጊዜ ለማየት በቃሁ…..፡፡ በሃይቁ ላይ በነጻነት የሚደንሱ የተለያዩ አሶች፤ደስ በሚለው የማያቃጥለው ሞቃት አየሯ እና ሰማይ ላይ በደስታ የሚንሳፈፉ የተለያዩ አእዋፋት……! ባላቸው አቅም ሁሉ በፍቅር አና በደስታ እንግዶቿን የሚያስተናግዱ ህዝቦቿ ልብ የሚመስጥ ነበር…..፡፡ በዚያን ጊዜ ከተማዋ አቅም እንደሌለው…. ወላጅ  እንደረሳው…. የህጻን ልጅ ቁምጣ እዚም እዛም የተቦጨቀ የአስፋልትና የጠጠር መንገዶች፤በአሁን ሰዓት መሃል ፒያሳ ጎዳናን በኩራት ተኮፍሶ የሚታየውን የገብርኤል ቤተክርስቲያን ጨምሮ በጅምር የቀሩ ጥቂት ህንጻዎች፤የሃዋሳ ሃይቀርን ተከትለው እንደሚታዩት ግዙፍ የሾላ ዋርካ ዛፎች….እድሜ የጠገቡ አብዛኛውን አሮጌ ቤቶችና የቆዩ ትንንሽ ሆቴሎች…..ወዘተ…. የነበራት ሃዋሳ…. ውበትዋ ማርኮኝ ከዛን ጊዜ ጀምሮ ቢያንስ በዓመት አንድ ጊዜ እየተመላለስኩ ደስታዬን አጣጥሜያለሁ……!፡፡ እነሆ ዛሬ ከሁለት አመት ቆይ በኋላ ዳግም ተመልሼ እዛው እገኛለሁ ፡፡ እጅግ በሚገርም ሁኔታ ከተማዋ ተለውጣለች… አምራለች…!፡፡ በየጊዜው ለውጥ አለ የተጀመሩ ህንጻዎች አልቀው ሌሎች ተጀምረዋል፡፡በ1960ዎቹ አካባቢ 6ኪሎ ሜትር ብቻ ይሸፍን የነበረው የአስፋከልት መንገድ ዛሬ 56.6 ኪሎ ሜትር ደርሷል፡፡ ትንሽ የነበረው ወስጥ ለውስጥ የተቦዳደሰ መንገዶችዋ ዛሬ በኮብል ድንጋይ 18 ኪሎሜትር ያህል ተነጥፏል፡፡ ከሌሎች መሰል የሃገራችን ከተሞች በአንጻራዊነት ሲታይ በእድሜ ትንሽ ብትሆንም ተፈጥሮም እያገዛት እጅግ በፍጥነት እያደገች….. የሃገር ውስጥ እና የውጪ ቱሪስቶች ፤ ኢንቨስተሮች ቀልብ እየሳበች የመጣች ከተማ ሆናለች ፡፡ ይሄንንም ተከትሎ በህዝቦችዋ እና አካባቢው ሊፈጠር የሚችለውን የተለያዩ አሉታዊ እና አዎንታዊ ገጽታዎች እንዳሉ ሆነው በዚህ አጋጣሚ በጣም የማደንቀው ደራሲ ጋዜጠኛ እና ሀያሲ አለማየሁ ገላጋይ ሶስተኛ ጆሮውን እና ሰስተኛ ዐይኑን ከፍቶ የታዘበውን የአሉታዊ ጓዳዋን በተለያዩ ጋዜጣና መጽሄት ላይ እያስነበበን ይገኛል ፡፡ ይሄን ለሱ እንተወውና ከተማዋ ውስጥ በነበረኝ ቆይታ ተዘዋውሬ ካየሁት ከሰማሁት፤ካነበብኩት በምስል በፎቶ ካስቀረሁት አዎንታዊ ገጽታዋ ለማለት ልሞክር፡፡
•••
ዛሬ የምናወራላት ሀዋሳ የዛሬ መጠርያዋን ከማግኘቷ ሀምሳ ዓመት በፊት “አዳሬ” የሚባል ስፍራ ነበር ትርጓሜውም “የግጦሽ መሬት” ማለት ነው እናም ከተማዋ የከተማ ወግ ስታገኝ ሀዋሳ ተብላ መጠራት ጀመረች ፡፡ ስሙ የተገኘው ከሃይቁ በመኮረጅ ሲሆን ቃሉም ሲዳምኛ ሲሆን “ሰፊ” ወይም “የተንጣለለ” እንደማለት ይሆናል ፡፡ ጂኦግራፊያዊ አቀማመጡ እና ከባቢያዊ ሁኔታውን ስንመለከት የዛሬው የሲዳማ ዞን  ወይም በቀድሞው የሲዳማ አውራጃ በስተሰሜን የሚገኝ ቦታ ሲሆን ከሻሸመኔ ከተማ አስተደቡብ አቅጣጫ ከአዲስ አበባ 275 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ትገኛለች ፡፡ከሀዋሳ በስተምእራብ የሀዋሳ ሃይቅ ተንጣሎ ሲገኝ በስተምስራቅ ደግሞ የወንዶ ገነት ተራራ አዘቅዝቆ ይመለከታታል ፡፡ ቦታው የስምጥ ሸለቆ አካል ሲሆን ልዩ ከሚያደርጉት መገለጫዎች ዋነኛው በዓመት ሁለት ጊዜ የዝናብ ወቅቶች ያለውና ለም መሬት በደን የተሸፈነ አካባቢ መሆኑ ነው፡፡
ይህ የዛሬዋን ሀዋሳ ነባራዊ ሁኔታ የለወጠው ታሪካዊ ክስተት የተፈጠረው በ1949 ዓም ነው ፡፡ ጉዳዩም የተከሰተው አጼ ሃይለስላሴ በ1949 ዓም በያኔው አጠራር የሲዳሞን ጠቅላይ ግዛት ለመጎብኘት በሚጓዙበት ወቅት የሃዋሳን አካባቢ ሲያቋርጡ በተመለከቱት የቦታው አቀማመጥና ተፈጥሮአዊ ጸጋ ተማረኩ፡፡ በወቅቱም የጠቅላይ ግዛቱ ገዢ  ለነበሩት ለደጃዝማጅ (በኋላ ራስ) መንገሻ ስዩም ትእዛዝ አስተላለፉ……“ በዚህ ቦታ ዘመናዊ እርሻ ልማት እንዲከናወን አዲስ ከተማም እንዲሰራ እንዲሁም በሃይቁ ዳር ቤተመንግስት እንዲሰራ…..” የሚል ትእዛዝ ነበር፡፡ በመሆኑም ራስ መንገሻ ስዩም ያስተዳድሩት ከነበረው የአርሲ ጠቅላይ ግዛት ተዛውረው የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛትን እንዲያስተዳድሩ ህዝቡንም እንዲያገለግሉ ሹመት አገኙ፡፡ ያኔ የጠቅላይ ግዛቱ ዋና ከተማ ይርጋለም ነበር ፡፡ ( በዚህ አጋጣሚ ከሃዋሳ ከተማ 43 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ የሚገኘው ይርጋለም ከተማ ብዙ ያልተዘመረለት የገጣሚና የውስጥ ቀዶ ሃኪም አብረሃም ፈለቀ (ቢላዋና ብዕር) የምትል የግጥም መድብል አለው)፤የነ ገጣሚ ደራሲ አብረሃም ረታ ፤የነ ገጣሚና  ጸሃፊ ተውኔት ደበበ ሰይፉ የትውልድ ከተማ ነው፡፡ ሄጄ የማየት እድሉ አጋጥሞኛል….! በተለይ ኪነ ጥበብን በሚያደንቅና  በዙርያው ላይ ላለ ሰው በሚያደንቃቸው የደራሲዎች ሃገር ሲገኙ ምን ያህል ደስታ እንደሚሰማው እኔ ምስክር መሆን እችላለሁ፡፡ እንደ አጋጣሚ ሁሉም በህይወት የሉም…… ምናልባት ወደፊት በተለይ ብዙ ስላልተዘመረለት ሁለገቡ ባለሙያ ስለ ዶክተር አብረሃም ፈለቀ ካየሁት ከሰማሁት ካነበብኩት ለማካፈል ለመጨዋወት እንሞክራለን) ፡፡
ራስ መንገሻ ይርጋለምን በሚያስተዳድሩበት ወቅት ከተማዋ ወደፊት ህዝቡ ሲጨምርና የማህበራዊ እኮኖሚያዊ ተቋማት ሲስፋፉ  አብሮ መስፋፋት ሊያስከትል የሚችለውን ችግር ካጠኑ እና ካስጠኑ በኋላ ለውሳኔ በማቅረብ በ1960 ዓም የሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት ዋና ከተማነት ከይርጋለም ወደ ሀዋሳ መዛወሩ እውን ሆነ…..፡፡ ይህ አጋጣሚ ለሀዋሳ እድገት ትልቅ እድል የፈጠረ ሲሆን ለይርጋለም ከተማ እድገት መጎተት መንስኤ ሊሆኑ ከሚችሉ ምክንያቶች እንደዋንኛው የሚቆጠር ይመስላል፡፡ በዚህም የተነሳ የሀዋሳ ከተማ ታሪክ ወደሌላ ምእራፍ ተሸጋገረ ፡፡
                                      2
         መጓዝ ማወቅ ነው…..! ነበር አይደል ያልነው….!? በስሚ ስሚ በወሬ ከመስማትና አንብቦ ከመረዳት የመለጠ ካሉበት ቄዬ ርቀው በመጓዝ ተፈጥሮን በማድነቅ ፤ የህብረተሰቡን ማህበራዊ አኗኗር ፤ባህል አስተሳሰብ ፤የአበላል ፤የአለባበስ፤ሃይማኖታዊ ስርዓት መረዳት ወዘተ….እቦታው ድረስ በመሆን አምስቱንም የስሜት ህዋሳት ከማሰራት ባሻገር ሀገሬ ብለህ የምትጠራት ሃገርህ ከመውደድ በዘለለ በእውቀት የተሞላ መረጃ እንዲኖርህ አሉታዊም ሆነ አዎንታዊ ገጽታውን ለይተህና ቀምረህ ለውጪው አለም እና ሀገር ውስጥ መረጃ እና ምስክር የሚሆን ካንተ በላይ ማን ያለ ይመስልሃል ? ማንም….!፡፡ እርግጥ ነው ሃገርህ ላይ በሚኖር መልካም አስተዳደር እጦት እሱን ተከትሎ በሚከሰት ሰው ሰራሽ ድህነት እንኳንስ ከሃገር ሃገር….መጓዝ ቀርቶ እንጀራ ፍለጋ ከቤት ወደ ስራ ቦታ መንቀሳቀስ አዳጋች የሆነበት ጊዜ ደርሰናል ፡፡ በዚህ በኩል በአንጻራዊነት ሲታይ የደርግ ዘመነ መንግስት የተሻለ መሰለኝ ቢያንስ በግዳጅም ቢሆን (ሀገርህን እወቅ) በሚል በየመስርያ ቤቱ በየትምህርት ቤቱ የሚቋቋም ክበብ እንደነበር…… እጅግ ከፍተኛ ትኩረት እንደሚሰጠው……ከፍተኛ ድጋፍም እንዳለው የሃገር ፍቅር ስሜት እንዲያድርብህ ትልቅ አስተዋጽኦ ነበረው……! ብዙ ታሪካዊ ቦታዎች ይጎበኙ ነበር እኔም ባለቀ ሰአትም ቢሆን የዚህ ፕሮግራም ተቋዳሽ ነበርኩ በርካታ ፓርኮችን ተፈጥሮአዊ መዝናኛዎችን ያየሁት ትምህርት ቤት በነበርኩበት ጊዜ ነው…..፡፡ አሁንም የለም ለማለት ባልደፍርም… ብዙ አልተሰራም ኧረ እንደውም አልተነካም….እርግጠኛ ነኝ ከሃገርህን እወቅና ጉዞ የበለጠ ሃይማኖታዊ ጉዞ እንደሚበልጥ አልጠራጠርም…. ያውም እንደዚህ አለም አንድ በሆነችበት ወቅት መረጃ እንደፈለገ ባስፈላጊው ሰዓት እየተገኘ ለምን እንዳልተሰራ ሁሉም ሊያስብበት…….፤ የሚመለከተው ክፍል ሊመልስ ይገባል ፡፡ ይልቅ ከደርዛችን ሳንወጣ ወደ ወጋችን እንመለስ….፡፡ መጓዝ ከአንድ ቦታ መንቀሳቀስ ትልቅ የውቀት ባህር ውሰጥ እንደመግባት ነው፡፡ በተለይ ለኪነጥበብ ሰው ይሄ አይነገርም……አንድ አጋጣሚ ላጫውታችሁ የሙዚቃ ደራሲ ገጣሚና ድምጻዊ ንዋይ ደበበ በአንድ ወቅት ከምኖርናት ከተማ ተገናኝተን በኪነጥነብ ዙርያ ሰፊ ጊዜ አሳልፈን ነበር ፡፡ ሃገር ውስጥ መጓዝ ተፈጥሮን ማድነቅ ታሪካዊ ቦታዎችን ማየት ይወዳል መውደድ ብቻ አይደለም በአንድ ወቅት ያጋጠመውን እንዲህ ሲል አጫወጠኝ…….፡፡
ከግቤ ባሻገር አለች እረ አንዲት ሰው
በፍቅር በናፍቆት ልቤን የምትወዘውዘው
አቦል ጀባ ብላ ቡናዋን ብቀምሰው
ልቤ ወደ ጂማ ሱስ አመላለሰው
ቤትሽ ጅማ ነው ወይ…….
ጅማ እንውረድ……… እያለ የአባ ጅፋርን ሃገር እያወደሰ የሚያቀነቅነውን ዘመን ተሸጋሪ የማይሰለች ዜማና ግጥም የደረሰው ከሃያ አንድ ዓመት በፊት ለኪነጥበብ ሙዚቃ ስራ በሄደበት አጋጣሚ በጉዞ ወቀት የጊቤ በረሃን አቋርጦ ጅማ ደርሶ ባለው ባየው ነገር ተገርሞ ተደምሞ…! ከዛም አልፎ ጅማ ድረስ ትርኢቱን ሊያሳዩ የሄዱትን የስራ ባልደረቦች ጨምሮ አንድ ታዋቂ የጅማ ሰው ቤት የእንኳን በደህና መጣችሁ የቡና ስነስርዓት በሚደረግበት ወቅት ቡናውን የምታፈላው የጅማ ቆንጆ ልጅ ውቧቷ ትህትናዋ ፤መስተንግዶዋ ስቦት እሷን ዋና ገጸ ባህሪ አድርጎ ጅማና አካባቢዋን የገለጸበትን ድርሰት እዛው ጽፎ እንደመጣ አጫውቶኛል፡፡ለዚህም ይመስለኛል በተለይ ተፈጥሮ….! ሃገርን እያወደሰ በስሜት  እያነሳ የጻፋቸው የሙዚቃ ግጥም ድርሰቶቹ ቀላልና የማይሰለቹ የሆኑት ወይም እውነት እውነት የሚሸቱት  እቦታው ከስሜት ሆኖ ስለሚጽፋቸው ይመስለኛል፡፡ ነውም ደግሞ…….እስቲ ልብ ብላችሁ አድምጧቸው፡፡
የነገር ዳርረዳርታዬ ወዲህ ነው ሃዋሳ ለዚህም ትመቻለች እውነት ትመቻለች….የነገ ሰው ይበለንና አጋጣሚዎችን እናነሳለን……..
                                          3
          ከምድር ወገብ 070 05' ሰሜን ላቲቲዩድ በ 380 35' ምስራቅ ሎንግቲዩድ በ1697 ሜትር የባህር ወለል አማካኝ ከፍታ ላይ 47.66 ካሬ ኪሎ ሜትር የቆዳ ስፋት ይዛ የምተገኘው የሃዋሳ ከተማ አመታዊ አማካኝ የዝናብ መጠኗ 945 ሚሜ አማካኝ የሙቀት መጠን 19.50 ሴንቲ ግሬድ አንጻራዊ የእርጥበት መጠኗ በዝናባማ ወቅት ከ70 እስከ 80 ፕርሰንት እንዲሁም በደረቅ ጊዜ ከ 40 እስከ 60 ፐርሰንት የሆነ ወይና ደጋ የአየር ንብረት ያላት ውብ ከተማ በአሁን ሰአት የህዝብ ብዛትዋ ወደ 300'000 ( ሶስት ሞቶ ሺ) እንደሚጠጋ ያገኘሁት መረጃ ያመለክታል፡፡ ይህንንም ተከትሎ ሃገራችን ካሉ መሰል ከተሞች በህዝብ ብዛት በ6ኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች ፡፡
ቀደም ሲል እንዳወራነው ሃዋሳ……. በተለይ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የአርቲስቶችን ቀልብ እየሳበች የመጣች ሃገር ሆናለች…..ሮጠው ማረፊያቸው እዛ ነው….. እውነት አላቸው…….   ከሁሉ በፊት ግን የሃዋሳ ውበት ያጣጣሟት እጅግ የተከበሩ የዓለም ሎሬት አርቲስት አፈወርቅ ተክሌ ናቸው ጊዜውም በ1963ዓም አካባቢ ከአንድ ጄነራል ጓደኛቸው ጋር ደቡብን ጎብኝተው ማምሻውን ሃዋሳ ደረሱ… ፡፡ እጅግ በጣም እንደተማረኩ ከሌሎች ቦታዎች ጸጥታው የሀዋሳ ሃይቅ ተፈጥሮአዊ አቀማመጥ ለስእል ስራቸው እጅግ አመቺ በመሆኑ ቀደም ሲል ሃገራቸው ላይ በየክፍለሃገሩ የስእል ስቱዲዮ የመክፈት ሀሳብ ስለነበራቸው ደቡብ ላይ ሀዋሳ ሀይቅ አካባቢ ቪላ አልፋ የመጀመርያ የስዕል ቤታቸውንም ገነቡ አርቲስቱ እጅግ በጣም የሚታወቁበትን ስዕል (ውቢት ሲዳማ) ደቡብን ብሎም ሃዋሳን የገለጹበት ስዕል እዚሁ ሃይቁ ዳር ሆነው እንደሰሩት ይነገራል (በዚህ አጋጣሚ ከ35 ዓመት በላይ ያስቆጠረው ቪላ አልፋ ቤታቸው አንዴ ሲወረስ አንዴ  ሲመለስላቸው ቆይቶ አሁን በሄድኩበት ጊዜ በህይወት ከማለፋቸው ጋር ተያይዞ እንደሆነም….. እንጃ…. ወይም በሌላ የቀድሞ ቤቱ እንደተሸጠ…. ፈርሶ…… ከፍተኛ ግንባታ እየተደረገበት መሆኑን አይቻለሁ… ሰምቻለሁ፡፡ ማን ሸጠው……?  እንዴት ተሸጠ….? ምናልባት ውስጡ የነበሩ ስዕሎች ካሉስ ማን ወሰዳቸው…..?፡፡ አዲስ አበባ ያለውን ለህዝብ እንደተናዘዙ አይተናል ይሄስ? ) ፡፡
          ይሄን ለአንባቢ እንተው እና ወደ ጨዋታችን እንመለስ፡፡
               የሃዋሳ ሃይቅ ልዩ ምትሃት አለው ጸጥታው የአእዋፋት ዝማሬ አሶች ዳንስ….. ልስልስ እያለ ከሀይቁ እየተነሳ የሚነፍስ ሙቅ አየር በቃ ምን ልበላችሁ ልዩ ነው..፡፡ ከሃዋሳ ከተማ በስተ ምዕራብ በ1680 ሜትር የባህር ወለል ከፍታ ላይ 94 ካሬ ሜትር የቆዳ ስፋት ይዞ የሚገኝ ሶሆን 8ኪሎ ሜትር አግድመት 16 ኪሎ ሜትር ርዝመት ዞርያው 49 ኪ.ሜትር አለው፡፡ ይህንን ተከትሎ በቀዳሚነት ለቱሪስት መስህብ በሚያመች መልኩ የዋቢ ሸበሌ ሆቴል ቁጥር አንድ እና ሁለት በማለት መገንባት የተጀመረ ሲሆን በአሁን አዓት አለም አቀፍ ስታንደርዱን የጠበቁ የሃይሌ እና ሌዊ እንዲሁም ሌሎች ሪዞርቶች ተገንብተው አገልግሎት እየሠጡ ይገኛሉ…፡፡ ሀይቁ 1363 ሚሊዮን ኪዩቢክ ሜትር ውሃ የመያዝ አቅም ሲኖረው ከፍተኛ ጥልቀቱ 13.5 ሜትር የሆነና ዓመታዊ አማካኝ የትነት መጠኑ 1736ሚ.ሜትር እንደሆነ ይገመታል፡፡ የሃዋሳ ሃይቅ በእትዮጵያ ስምጥ ሸለቆ ከሚገኙ ሃይቆች በመጠን አነስተኛ ነገር ግን በጣም ምርታማ የሆነ ነው፡፡ ሃይቁ በውስጡ ለሚገኙት ስድስት አይነት የዐሳ ዝርያዎች በምግብነት የሚውሉ ፓይቶ ፕላንክተን(100 ዓይነት ዝርያ)እና ዙ ፕላንተን የተባሉ ተክሎችን የያዘ ሲሆን በሃይቁ ላይ በዓለም በጣም አነስተኛ የሆነውን ባለ አበባ ተክል (ወልፊያ አሪዛ) ጨምሮ ብዛት ያላቸው የአሳ ዝርያዎች ይገኛሉ፡፡ ሀይቁ ሁለት በእትዮጵያ ብቻ ሚገኙና ሰባት በአፍሪካ ከፍታማ ስፍራዎች ላይ ብቻ ያሉ የአእዋፍ ዝርያዎችን አካቶ ብዛት ላላቸው አእዋፋት የመራቢያ የምግብ ምንጭና መጠለያ በመሆን በሃገራን ውስጥ ከሚገኙ 31 ከፍተኛ የአእዋፋት ክምችት ካላቸው ቦታዎች ውስጥ አንዱ ነው፡፡ በተጨማሪም ሳነብ እንዳገኘሁት መረጃ ከአቢጃታ ሃይቅ መድረቅና ቀውስ ነተያያዘ በተከሰተው የአሳዎች መጥፋት ሳቢያ ብዛት ያላቸው የወፍ ዝርያዎች በመፍለስ የሃዋሳ ሃይቅን መጠግያ አድርገውታል፡፡ለዚህም ነው እኔንም ጨምሮ በርካታ ቱሪስቶችን፤ አርቲስቶችን ለመሳብ የቻለው ሃዋሳ በርካታ ጊዜ መመላለሴን አወራን አይደል…? አዎ አንድ ምሽት ሃይቁ ዳር ቆጭ ብዬ የቀኗ ጸሀይ የቀን ውሎዋን አጠናቃ ጠልቃ ከመሰወሯ በፊት ወቃማ ብርኃኗን እየሰጠችኝ በልዩ ፍቅር እያስታወስኩ የጻፍኳትን ግጥም ጀባ ልበል…….
                  
አዋሳ
አንቺ አዋሳ
ውበት ስምሽን ሳነሳ
በፍቅር ሐይቅ ላይ በቅዳሜ
አጀብ ጉድ እያልኩኝ ተደምሜ
ካሞራ ገደል ስር እጆቼን ዘርግቼ
ለጥሜ እርካታ ውብ አየርሽን ግቼ
ሀሳብ ጭንቄን ላንቺ ትቼ
ቆይቼ ………ቆይቼ
ድንገት ውልብ ቢለኝ
የወፎችሽ ዜማ ቀስቅሶኝ
ሲያሽካኩ በደስታ አሶች ሲደንሱ
ከሀይቅሽ መንደር ላይ ሲፈሱ
ጦጣና ጉሬዛ
ጉሬዛና አባኮዳ
ፍቅር ሰርተው እንደዋዛ
የወግ ጨዋታቸው ለዛ
የደስታዬን እርካብ ላይዘሉ
ቢደክሙ
ከዋርካሽ ጥላ ስር አርፌ
ጭ…….ልጥ ብዬ በሐሳብ ከንፌ
ታቦር ተራራሽ ከሩቁ
ቆሞ ከነግርማ ሞገሱ
‘ና………ወዲህ’ እያለኝ
ሚስጥርሽን ሊያወጋኝ
ብወጣ ካናቱ
ከዙፋኑ
ደስታው አሰከረኝ
እልፍ መንደርሺን ጀባ ቢለኝ፡፡
ሐዋሳ
    መሀል ከተማሽ ከፒያሳ
ዘር ቀለም ሀይማኖት ሳይነሳ
ካ‘ረብ ሰፈር ከደመቀው
  ዙርያ ገባ ከቀለጠው
ቼ……..ብዬ ስሜቴን ጋልቤ
ጋልቤ ጋልቤ ፈረሴን ኮርኩሬ
 በምሽት ጨረቃ "በሌንቦ" ጨፍሬ
ነፍሴን ወድያ ማዶ በደስታ አጥሬ
እንዳልቀር በዛው ለከርሞዬ
ገብርኤል ከመቅደሱ ተሳልሜ
ውቅሮና ኮረም
ሰፈረ ሰላም ከዳር ስሩ
    ተከብቤ ከመንደሩ
የቱን ትቼ የቱን ላንሳሽ አለሜ
  ቃላት ጠፋብኝ እኮ ላ‘ቅሜ፡፡
እንዲህ ነሽ እንግዲህ አንቺ
እንደኔ ፍቅሩን ለቀመሰ ስትመቺ
እንመጣለን ደግሞ ባ‘መቱ
እንደ ባህር አድማስሽ ሰፍቶ
ውበትሽ እንዳ‘በባ ፈክቶ
"ዳኤ ቡሹ" ልትይን በፍቅርሽ
የተስፋን አንቀልባ ተሸክመሽ፡፡
* * *
ሐምሌ 18/1999 ዓም
ሐዋሳ ሐይቅ ዳር

No comments:

Post a Comment